Friday, March 7, 2014

ቤት ተከራዩ እግዜር



እግዜር፡- እንዴት ዋልሽ ልጄ? በር ላይ ያለውን “የሚከራይ ቤት አለ” የሚል ማስታወቂያ አይቼ ነው ያንኳኳኹት፡፡ ለልጄ ቤት      እየፈለግኹ ነው፡፡
እኔ፡- ቆንጆ ቆንጆ የሚከራዩ ክፍሎች አሉኝ፡፡ ዋጋቸውም በጣም ቅናሽ ነው፡፡
እግዜር፡- አይ፣ እኔ እንኳን እንደው ሙሉውን ግቢ መግዛት ነበር የምፈልገው?
እኔ፡- እምምምም… በእውነቱ መሸጥ የምፈልግ እንኳን አይመስለኝም፡፡ ማየት ከፈለግኽ ግን ግባና ክፍሎቹን ተመለካከት፡፡
እግዜር፡- እሺ፡፡
እኔ፡- አንድ ወይም ኹለት ክፍል ላከራይኽ እችላለኹ፡፡
(ቤቱን ጥቂት እየተዟዟረ ሲያይ ቆየና)
እግዜር፡- ቤቱን በጣም ወድጄዋለኹ፡፡ ኹለቱንም ክፍሎች እወስዳለኹ፡፡ ሌላ ቀን ደግሞ ጥቂት ተጨማሪ ክፍሎች ትሰጪኝ ይኾናል፡፡
እኔ፡-  ተጨማሪ ክፍሎችን ብሰጥኽ ደስ ይለኛል፡፡ ግን ደግሞ አየኽ፣ ለራሴም ትንሽ ስፍራ ያስፈልገኛል፡፡ ለዚያ ነው፡፡
እግዜር፡-  ይገባኛል፡፡ ተረድቼሻለኹ፡፡ ችግር የለም፤ መታገሥ እችላለኹ፡፡ ያን ያኽል የሚያስቸኩለኝ ነገር የለም፡፡
እኔ፡- ቆይ… አንድ ተጨማሪ ክፍል ልሰጥኽ ግን እችላለኹ፡፡ ማለቴ፣ ያው ያን ያኽል ብዙ ክፍል ስለማያስፈልገኝ… 
እግዜር፡- በጣም አመሰግናለኹ! እንደ ነገርኹሽ ቤቱን በጣም በጣም ወድጄዋለኹ፡፡ (ፊቱ ላይ የሕጻን ልጅ ፈገግታ ይጫወታል)
እኔ፡- እውነት ለመናገር፣ ቤቱን ሙሉ ብሰጥኽ ደስ ይለኛል፡፡ ግን አየኽ አንዳንድ ነገሮች ላይ እርግጠኛ አይደለኹም፡፡
እግዜር፡- ችግር የለም፡፡ አትጨነቂ፡፡ ቀስ ብለሽ ታስቢበታለሽ፡፡ እኔ ቤቱን ሙሉ ብገዛውም አንቺን ከቤትሽ አላስወጣሽም፡፡ ልጄና አንቺ ሰፋ ብላችኹ ትኖሩበታላችኹ፡፡ የአንቺ የእኔ ይኾናል፤ የእኔም የአንቺ ይኾናል፡፡ ምንም ችግር የለውም፡፡ እንዲያውም የሚገርምሽ ነገር ያኔ ቤትሽ እስከዛሬ ከነበረው ስፋት ይልቅ ይሰፋሻል፡፡
እኔ፡- እ…?! አልገባኝም፡፡
እግዜር፡- አዎን፣ አውቃለኹ፡፡ ይኽ አንቺ ራስሽ የምትደርሺበት ነገር ነው እንጂ እንዴት እንደሚኾን ላስረዳሽ የምችለው ነገር        አይደለም፡፡ የሚኾነውም ቤቱን ሙሉ በሙሉ ለእኔ ከተውሽልኝ ነው፡፡
እኔ፡- እ…እም… ማለቴ… እርግጠኛ መኾን አልቻልኹም፡፡ ትንሽ ሪስኩ በዛብኝ፡፡
እግዜር፡- ዐውቃለኹ፡፡ ይገባኛል፡፡ ግን እስኪ ሞክሪኝና እዪው፡፡ Try me.
እኔ፡- እም… እስኪ ቆይ… በደንብ ላስብበትና እነገርኻለኹ፡፡
እግዜር፡- ችግር የለም፡፡ አትጨነቂ፡፡ ዝግ ብለሽ አስቢበት፡፡ እኔም እስካኹን የሰጠሸኝን ይዤ መጠበቅ እችላለኹ፡፡ እንደነገርኹሽ ቤቱን በጣም ወድጄዋለኹ፡፡ እስካኹን በሰጠሽኝም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ 

(Source:- Peter Hannan (SJ). The Nine Faces of God)

1 comment: