አሁን ዲጄው ከድምጽ ማጉያው ጋር ተቧድኗል፡፡ ታዳሚዎቹ ደግሞ በአንድ ላይ ሆነው በባዶ ጉሮሮ እየተፎካከሩት ይገኛሉ፡፡ እንቅልፌን አባረሩብኝ፡፡ “ምነው ጉሮሯችሁ እንደ አክርማ ከሁለት በተሰነጠቀ!” ብዬ ልራገም አማረኝ፡፡ ግን ያን የመሰለ የእናቴን ጉርሻ ሊቀበል የነበረ አፌ እንዲህ ያለ መራራ ነገር አይመጥነውም ብዬ ተውሁት፡፡ ደግሞ የእናቴ መንፈስ ሰምቶኝ ሰዎቹን በሙሉ ጉሮሮ አልባ ቢያደርጋቸውስ?
እነሆ በአንድ ሌሊት እንቅልፌን ለሁለተኛ ጊዜ ተነጠቅሁ፡፡ ወይ ነዶ! የብስጭቴ ብዛት ውስጥ እግሬ ድረስ ዘልቆ ስለተሰማኝ ነው መሰለኝ ልቤ በኃይል ትመታ ጀመር፡፡ ውስጥ እግርና ልብ እንዴት ይገናኛሉ? የሚለው ጥያቄ ለሥነ ሕይወት ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች ወይም ተማራሪዎች የቤት ሥራ ይሁናቸው፡፡
ሞባይሌን አየሁት፡፡ ከሌሊቱ 7፡13 ደቂቃ ይላል፡፡ ነገ 4፡00 ላይ የምፈተነው ፈተና አለኝ፡፡ ምንም እንኳ የምማረው ለሁለተኛ ዲግሪዬ ቢሆንም ቅሉ ውጤቴ ላይ ቀልድ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም አሁን ከምሠራበት መሥሪያ ቤት አሰልቺ ልማታዊ ስብሰባና አቆርቋዥ የቢሮ ፖለቲካ ልላቀቅ የምችለው ይህቺን ዲግሪዬን ስይዝ ብቻ እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ እርግጥ ነው ሰሞኑን አብዛኛውን ከዕንቅልፌ፣ ጥቂት ጥቂት ደግሞ ከሻይ ሰዐቴም፣ ከቢሮ ወሬ ሰዐቴም፣ ከታክሲ ላይ ቆይታዬም እየቀነጣጠብሁ ጥሩ ስቸክል ከርሜያለሁ፡፡ ትምህርቱ ደግሞ ደስ ይላል፡፡ A ማምጣት እንዳለብኝ ከራሴ ጋር ተስማምተናል፡፡ ዛሬ ሌሊት እስከ 9፡30 ድረስ ተኝቼ ከዚያ በኋላ ያሉትን ሰዐታት ለመጠቀም አስቤ ነበር፡፡ እድሜ ለጎረቤቶቼ እነሆ ለሊቷ ዓይኔ እያያት ሔደች፡፡ ራሴ ይወቅረኝ ጀመረ፡፡ እማማ እልፍነሽ መውጣታቸውን ማየቴ አደፋፈረኝና የመጣው ይምጣ ብዬ መብራቱን አበራሁት!
እንደምንም ራሴን አበረታታሁትና ከአልጋዬ ወርጄ ፊቴን ታጠብሁ፡፡ ወረቀቶቼን ከቦርሳዬ ውስጥ አውጥቼ አልጋዬ ላይ ቁጭ አልሁ፡፡ አንድ ሰዐት ያህል እንዳነበብሁ ዓይኔ ይቆጠቁጠኝ ጀመር፡፡ ዕንቅልፌ እንዳያሸንፈኝ ብዬ ከአልጋዬ ወረድሁና ቆሜ ማንበብ ጀመርሁ፡፡ ብርዱ ሊሰማኝ ሲጀምር አልጋ ልብሱን ለብሼ አልጋ ላይ ቁጭ አልሁ፡፡ የዲጄው ሙዚቃ እየቀነሰ ሔዷል፡፡
* * * *
የድሮ ትምህርት ቤታችን ውስጥ ነን፡፡ አባዬ የገዛልኝን አዲሱን ሮዝ ቀሚሴን ለብሻለሁ፡፡ የዓመቱ መጨረሻ ነው፡፡ ሁላችንም ወላጅ አምጥተናል፡፡ የመረብ ኳስ ሜዳችን ላይ የክፍል ዴስኮቻችን ወጥተው ወላጆቻችንና እኛ ተደርድረንባቸዋል፡፡ ከየክፍሉ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ ተማሪዎች እየተሸለሙ ነው፡፡ የኛ ክፍል ተራ ደረሰ፡፡ የአካባቢ ሳይንስ ቲቸራችን መነጽራቸውን አስተካከሉና
“ከሦስተኛ ኤ ተማሪ ምሥራቅ ቢተርፍ ሦስተኛ!” በማለት ጮሁ፡፡
ወላጆቻችን አጨበጨቡ፡፡
ወንዳታ! ሦስተኛ አልወጣሁም ማለት ነው፡፡ አባባ ደግሞ ከአንድ እስከ ሁለት ከወጣሽ የቦሊ ቦሊ ኳስ እገዛልሻለሁ ብሎኛል፡፡
ጓደኛዬ ምሥራቅ ሽልማቷን ተቀብላ ተመለሰች፡፡ ሱዚና ገመድ ዝላይ የሚችላት የለም፡፡ ቦሊ ቦሊ ግን እኔ እበልጣታለሁ፡፡
“ተማሪ ደቻሳ ግርማይ ሁለተኛ!” የስ! አንደኛ ነው የወጣሁት ማለት ነው!
ደቻሳ ስዘልል አየኝና አኮረፈ፡፡ ስለበለጥኩት ነው፡፡ ግን ሽልማቱን ሔዶ ወሰደ፡፡
“ተማሪ በፍቅር አዘዘ አንደኛ! አጨብጭቡላት!” ሰዉ ሁሉ አጨበጨበልኝ፡፡ ምሥራቅ ግን አላጨበጨበችልኝም፡፡ እኔ ግን አጨብጭቤላት ነበረ፡፡
አባዬ ዕቅፍ አድርጎ ሳመኝና “ሒጂ ሽልማትሽን ውሰጂ፡፡” አለኝ፡፡
“አባዬ የቦሊቦሊ ኳሴን ትገዛልኛለህ አይደል?”
“እሺ፡፡ እሱ በኋላ ይደርሳል፡፡ አሁን ሒጂና ተሸለሚ፡፡”
ዳይሬክተራችን በቢጫ ወረቀት የተሸፈነ ነገር ይዘዋል፡፡ ለኔ ነው፡፡ ፈገግ ብለው እያዩኝ ነው፡፡ አካባቢ ሳይንስ አስተማሪያችንም እያጨበጨቡልኝ ነው፡፡ መድረኩ ጋር ልደርስ ነው፡፡ ከኋላዬ የነበረው ጭብጨባ በድንገት ጸጥ አለና “ተንሥኡ ለጸሎት!” የሚል ትእዛዝ ሰማሁ፡፡ ወደኋላዬ ዞር አልሁ፡፡
የእማማ እልፍነሽ ቤተክርስቲያን ዲያቆን ከሞት ለመቀሰቅስ በሚመስል ጩኸት ሽልማቴን ነጠቀኝ፡፡ እስኪ ምናለ በሕልም እንኳ ብሸለምበት?
“እግዚኦ ተሣሃለነ፡፡” ሌላ ድምጽ ተቀብሎ አካባቢውን አንቀጠቀጠው፡፡ ከመሬቷ በስተቀር ሁሉ ነገሯ ቆርቆሮ የሆነችው ቤተክርስቲያኗ አናቷ ላይ የሰቀሉባትን ይህን አገር ገልብጥ ድምጽ ማጉያ እንዴት እንደቻለችው አላውቅም፡፡ "ቆይ ደግሞ “ለጸሎት ተነሡ!” የሚለው ትእዛዝ ቤተክርስቲያን ውስጥ ላለሰው እንጂ እሥራ ላይ ውሎ ደክሞት ቤቱ አልጋ ላይ ማንንም ሳያስቸግር የተኛ ሰውን ነው እንዴ?" ተነጫነጭሁ፡፡ ወረቀቶቼ አልጋው ላይ ተበታትነዋል፡፡ ደብተሬም መሬት ላይ ወድቋል፡፡ ወይ ነዶ!
ሰዐት አየሁ፡፡ ከሌሊቱ 10፡10 ይላል፡፡
“ሰላም ለኵልክሙ!” ቄሱ ቀጠሉ፡፡ ወይ ሰላም! አጠገቤ ቢሆኑ ኖሮ ብዬ ተመኘሁ፡፡
“ለእኔ አሁን ሰላሜ እንቅልፌ ስለሆነ አይበጥብጡኝ! አይጩሁብኝ! ልተኛበት! እኔ እንደእርስዎ በወር ሁለት ሳምንት ሳይሆን በወር አራት ቀናት ብቻ እንዳርፍ የተፈቀደልኝ ግብር ከፋይ ዜጋ ነኝ፡፡ እሑዴን አይሸራርፉብኝ፡፡ እማማ እልፍነሽን ከሆነ እርስዎ ጋር ስለሆኑ በሹክሹክታም ቢናገሩ ይሰሙዎታል፡፡ እኔን ለእንቅልፌ ይተዉኝ፡፡ አሁን ጸሎትዎን ለመካፈልም ሆነ የድምጽዎን መረዋነት ለማድነቅ ጊዜዬ አይደለም፡፡” እላቸው ነበር፡፡
ዕንቅልፌ ሲሸሽ ጥሎት በሔደው የድካም ጓዝ ሰውነቴ ደቀቀብኝ፡፡ ትራሱ ቆልምሞኝ ነበረ መሰለኝ አንገቴን በጣም አመመኝ፡፡ አጠገቤ የነበሩትን ወረቀቶች በማንሣት ጥናቴን ለመቀጠል ሞከርሁ፡፡ ከአንድ ሰዐት በላይ ግን መቀጠል አልቻልሁም፡፡ ዓይኖቼ እጅግ ያቃጥሉኝ ጀመር፡፡ ቢያንስ አእምሮዬ በቂ ዕረፍት ካገኘ እስከዛሬ ያጠናሁትን ፈተና ላይ ንቁ ሆኜ እንደምሠራ ራሴን አባበልሁትና የሔደውን እንቅልፌን ለመከተል ቆረጥሁ፡፡ ጠዋት ዕንቅልፍ እንዳይጥለኝም ስልኩን ዐላርም ሞላሁት፡፡ እግረመንገዴንም አሁን 11፡05 መሆኑን አየሁ፡፡ የመስጊዱ ሙአዚን በአረብኛ “ከእንቅልፍ ሶላት ይሻላል!” ሲሉ መጣራት ጀምረዋል፡፡ እኔ ግን ለጊዜው አምላኬን ከጸሎት ይልቅ በሕልም ውስጥ ማየትን መርጫለሁ፡፡ ስለዚህ ልተኛ ነው፡፡ አልጋልብሱን ወደፊቴ ሳብሁትና ተሸፋፈንሁ፡፡
* * * *
“ምእመናን ሙሽሮቹ እየገቡ ስለሆነ እልል በሉ! እልል በሉ! እልልልልልልልልልልልልልልልል!”
“በጽሐ መርዓዊ ፍሥሐ ለኵሉ
በሰላም ጻኡ ተቀበሉ፡፡”
ወይ ሰላም! የትልቁ ቤተክርስቲያን ትልቁ ድምጽ ማጉያ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ሁለት ሰዎች ከሁለትነት ወደአንድነት በመምጣት ላይ በመሆናቸው እኔ በምንም ምክንያት ለብቻዬ እንቅልፌን ማጣጣም እንደማልችል ነገረኝ፡፡ ወይ ጣጣ! አሁን እነዚህን ሰዎች ለማጋባት ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ያለው ሰው እልል ካለ አይበቃም? ቤታችን ያለን ሰዎች ሁሉ አልጋችን ውስጥ ሆነን እልል ማለት ይጠበቅብናል? ወይስ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ የሚደረገውን ነገር በሙሉ እኛ ልንሰማው ያስፈልጋል? እንዴ መስማት ከፈለግን እንመጣ የለም እንዴ የምን ረብሻ ነው?
የእማማ እልፍነሽ ቤተክርስቲያን ካህን ደግሞ “ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ” እያሉ ደመቅ አድርገው ያዜሙ ጀመር፡፡
ሦስቱም ድምጽ ማጉያዎች አንድ ላይ ሲጮሁብኝ ራሴ ዉዉዉ... ይልብኝ ጀመር፡፡
ተኝቶ ከማዳመጥ ውጪ ምንም ማድረግ አልቻልሁም፡፡ ሦስቱንም በደነዘዘ አእምሮ ማድመጥ ጀመርሁ፡፡ አስራ አንድ ሰዐት ተኩል አካባቢ ሙአዚኑ ዝም አሉ፡፡ አሁን የሁለቱ ቤተክርስቲያኖች ድምጽ ማጉያዎች እሪታ ብቻ አካባቢውን ተቆጣጥሮታል፡፡
“ተሣሃልከ እግዚኦ ምድረከ!”
“ሠርዐ ለነ ሰንበተ ለዕረፍተ ዚአነ ፍሥሐ ወሰላም ለእለ አመነ፡፡”
እንቅልፍ በዓይኖቼ ሊዞር አልቻለም፡፡ ይህቺ ሞገደኛ ውስጤ ሒጂና “እኔን ዕንቅልፌን እየነሣችሁኝ እናንተ ሰንበት ለዕረፍት ነው ብትሉ እንዴት ላምናችሁ ይቻለኛል?” በያቸው አለችኝ፡፡ እኔ ግን ዐቅሜን ስለማውቅ ለሌሊት እንቅልፍ ብዬ የቀን ሕይወቴን መቃብር አላወርዳትም ብዬ ተውሁት፡፡
ኪዳኑ አለቀ፡፡ ቅዳሴ ቀጠለ፡፡
“ኵሉ ዘገብራ ለጽድቅ ጻድቅ ውእቱ ወዘያከብር ሰንበተ፡፡”
…
“ጻኡ ንኡሰ ክርስቲያን፡፡”
ሰዐቴን አየሁት፡፡ 1፡15፡፡ ፈተናዬ ሊጀመር ሁለት ሰዐት ከ45 ደቂቃዎች ይቀሩታል፡፡ እነዚህን ሰዐታት እንኳ ብተኛ ንቁ እሆን ነበረ፡፡ ከመንጋጭላዬ የግራ ጎን አንሥቶ እስከመሐል አናቴ ድረስ እየወጋኝ ነው፡፡ ራስ ፍልጠት የሚባለው መሆን እንዳለበት ገመትሁ፡፡ ጨጓራዬም ክፉኛ መገለባበጥ ጀምሯል፡፡ በጊዜ በወተት ካላበረድሁት እንደተለመደው ሳምንት ሊያስተኛኝ መሆኑ ነው፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ሔጄ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ትንሽ ብተኛስ? እንዲያውም ከሸምሱ ሱቅ የላስቲክ ወተት እገዛና እሱን መንገድ ላይ ጠጥቼ እሔዳለሁ፡፡ ከአልጋው ላይ በፍጥነት ወረድሁና ማታ በያቅጣጫው የወረወርኳቸውን ልብሶቼን ከያሉበት ጠርቼ ለባበስሁ፡፡ ጫማዬን አስሬ ቀና ስል የማየው ነገር ሁሉ ነጭ ሆነብኝ፡፡ አዞረኝ፡፡ ቶሎ ብዬ ቁጭ አልሁ፡፡
የእማማ እልፍነሽ ዲያቆን “የተቀመጣችሁ ተነሡ!” ሲል ሰማሁት፡፡
ወይ መነሣት!
ለጥቂት ደቂቃዎች እዚያው ባለሁበት ተቀመጥሁና መለስ እንደማለት ሲልልኝ ቀስ ብዬ ተነሣሁና በሩን ቆልፌ ወጣሁ፡፡
ክሊኒኩ ጋር ስደርስ የሆነ ነገር መሬት ላይ ወድቆ ተመለከትሁ፡፡ ጎንበስ ብዬ አየሁት፡፡ ጠላታችሁ ወከክ ይበል ልቤ ወከክ አለ፡፡ መቶ ብር! እንዴ! ሌሊቱን ሙሉ በእርሱ ስም እንቅልፍ ሲነሱኝ ያደሩትን ተመልክቶ አምላክ ለካሳዬ የሚሆን ነገር አዘጋጀልኝ፡፡ ብድግ አደረግኋት፡፡ ቀና ስል ግን ሰማይ ምድሩ ተደባለቀብኝ፡፡ ምድሪቷ ከሥሬ ከዳችኝ፡፡ ጸጥታ፡፡
* * * *
“በፍቅር! በፍቅር!”
ነቃሁ፡፡ ክንዴ ላይ ግሉኮስ ተቀጥሎልኛል፡፡ ተርፌያለሁ ማለት ነው፡፡ ነጭ ገዋን የለበሰ ረዥምና ወፍራም ሰው አጠገቤ ቆሞ ይጠራኛል፡፡ በዓይን አውቀዋለሁ፡፡ የክሊኒኩ ነርስ ነው፡፡
“አቤት”
“ምን ሆነሽ ነው፡፡”
“አዙሮኝ፡፡”
“ስትወድቂ እኔ ከኋላሽ ነበርሁ፡፡ አንሥቼሽ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያምሽ ነበር እንዴ?”
ከጨጓራ በስተቀር የማውቀው ሌላ ሕመም እንደሌለብኝና ሌሊት በእንቅልፍ እጦት እንዴት እንደተሰቃየሁ ነገርሁት፡፡ ፊት ለፊቴ የተሰቀለውን የግድግዳ ሰዐት ተመለከትሁት፡፡ 3፡00፡፡ የአራት ሰዐቱ ፈተናዬ ትዝ አለኝ፡፡ እንደምደርስ አሰብሁ፡፡ አሁን ራስምታቱ ቀለል ብሎልኛል፡፡ ጸጥ ብሏል፡፡
“ታድለህ!” ብዬ ልናገር ስል የቤቱ የፍሎረሰንት መብራት እንደጥንዚዛ መጮህ ጀመረ፡፡
“Great! መብራት መጣ ማለት ነው፡፡” አለ፡፡
በዚያው ቅጽበት ከጎረቤት “ኢየሱስ ጌታ ነው! ኢየሱስ ጌታ ነው! እልልልልልልል!” ተባለ፡፡ አዲሷ የሰፈሬ ፕሮቴስታንት ቸርች ምእመናን ናቸው፡፡ ኪይቦርዱ አጉረመረመ፡፡ አስመላኪው ምእመናኑን ለዝማሬ ጋበዘ፡፡ እስከ ሰማይ ድረስ በእነርሱ ምስጋና ምድርን እንደ ብረት ድስት ክድን እንደሚያደርጓት መንፈሳዊ መፈክር አሰማ፡፡
“አሜን! ሀሌሉያ! እልልልል!” ተባለ፡፡ ከዚያም አካባቢው ይቀወጥ ገባ፡፡
“የነፍሴ ወዳጅ አንተ በፍቅርህ ልቤን ታሳርፋለህ፡፡”
“እልልልልልል…..!”
እያሉ ይዘምሩ ጀመር፡፡ የጭብጫቦውና የእልልታው ሱናሚ የክሊኒኩን የጭቃ ግድግዳ ያናግረው ገባ፡፡ ነርሱ ምንም እንዳልተፈጠረ ሥራውን ቀጥሏል፡፡ ያው በፊዚካል ምናምን እቋቋመዋለሁ ብሎ ይሆናል፡፡ እኔ ግን “ጃፓንን ያየ በሱናሚ አይቀልድም፡፡” ብዬ የመሐሙድን “ዐቅምን ዐውቆ መኖር ጥሩ ነው፡፡” እየዘፈንሁ ከአልጋው ዱብ፡፡ የምሬን ነው የምላችሁ የሃይማኖት ድርጅቶች በሙሉ እኔ እንዳልተኛ በጠላትነት የተሰለፉብኝ መሰለኝ፡፡ እንዴ! እነርሱ ስለ እረፍታቸው የሚያመሰግኑት ሌላ ሰው ዕረፍት እየነሱ ነው እንዴ?
ከክሊኒኩ ስወጣ አያቴ ዳዊት ሲደግሙ “መኑ ይሁበኒ ክንፈ ከመ ርግብ እስርር ወአእርፍ” ይሉ የነበረው ትዝ እያለኝ ነበር፡፡
በርሬ አርፍ ዘንድ እንደርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ (መዝ. 55፣6)፡፡