በ1861
ዓ.ም. ገደማ በምዕራብ ሸዋ ሑሩሙ በምትባለው ስፍራ ባርያ ነጋዴዎች አንድ “ሒቃ አዋጂ” (ሒቃ ማለት በኦሮምኛ ተርጓሚ ማለት
ነው፡፡) የሚባል የ14 ዓመት ታዳጊ ጠልፈው ወደ ምፅዋ ወሰዱት፡፡ ስምንት ጌቶችም በየተራ ተቀባበሉት፡፡ ገና በአራት ዐመቱ
አባቱን ያጣ ልጅ እንዲኽ ያለ የመከራ ጽዋ ሲደመርበት ምን ያኽል ሕይወት መራር እንደምትኾንበት የደረሰበት ያውቀዋል፡፡
ምፅዋ
ሲደርስ (ደግ ሰው አይጥፋ!) የስዊድን ሚሲዮናውያንን አገኘና እነርሱ ከባርነት ነጻ አወጡት፡፡ በ1864 ዓ.ም. ዕለተ
ትንሣኤም ጥምቀተ ክርስትናን ተቀብሎ “ኦኔሲሞስ” የሚል የክርስትና ስም ተሰጠው፤ ትርጓሜውም በግሪክኛ “ጠቃሚ” ማለት ነው፡፡
ስዊድናውያኑ
ይኽን ልጅ ትምህርት ቤታቸው ውስጥ ትምህርት እንዲከታተል አደረጉት፡፡ ያሳይ የነበረውን የትምህርት ብቃትም ተመልክተው ለበለጠ
ትምህርት ወደ ሀገረ ስዊድን ላኩት፡፡ እዚያም በትምህርት ረዘም ላለ ጊዜ ከቆየ በኋላ በ1874 ወደ ምፅዋ በመመለስ ምሕረት ኃይሉ የተባለች ቆንጆ አግብቶ ምፅዋ ውስጥ ይገኝ በነበረ ትምህርት ቤት ሲያስተምር ቆየ፡፡
ቀስ
ብሎም በ1883 ዓ.ም. ገደማ መጽሐፍ ቅዱስን ከአስቴር ገኖ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር በመኾን ወደ ኦሮምኛ መተርጎም ጀመረ፡፡
በአራት ዓመታት ውስጥም ይኽ የኦኔሲሞስ ቡድን ሐዲስ ኪዳንን ተርጉሞ ለማውጣት ችሎ ነበር፡፡ ይኽ ቡድን በአቀባይ ጽሑፍነት
የተጠቀመው “የአባ አብርሃም” ወይም በቅጽል ስማቸው “አባ ሮሜ” በመባል የሚታወቁት ያዘጋጁትን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር[1]፡፡ የተጠቀሙት
ፊደልም ኢትዮጵያዊውን ፊደል ነው፡፡ ይኹን እንጂ፣ በትርጉም ሥራው ወቅት ኦኔሲሞስ የአባ አብርሃምን ትርጉም ትክክለኛነት
ለማረጋገጥ በስዊድንኛ የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስም ይጠቀሙ ነበር፡፡ እንዲኽ ባለ ጥረትም ተተርጉሞና ታትሞ በ1892 ዓ.ም.
ገደማ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮምኛ ታትሞ ለአንባቢ ቀረበ፡፡ በ1976 የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ሌላ
የአሮምኛ መጽሐፍ ቅዱስ እስኪያሳትም ድረስም ለ94 ዓመታት ያኽል ሕዝቡን አገለገለ፡፡
“ሒቃ”ም
እንደስሙ ተርጓሚ ኾኖ ለ94 ዓመታት ኢትዮጵያውያን የሚበሉትን ፍሬ አፈራላቸው፡፡ ጠቃሚያቸውም ኾነ፡፡[2]
[1] በነገራችን ላይ፣ አባ ሮሜ ይኽንን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ከአረብኛ ተርጉሞ ለማቅረብ
10 ዓመታት (ከ1800-1810) ፈጅቶባቸዋል፡፡
[2]ዋቢዎች፡-
ኃይለ ኢየሱስ እንግዳሸት፡፡
“የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በኢትዮጵያ ዐጭር ቅኝት፡፡” መድበለ ጉባኤ፤ የምዕተ ዓመቱ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት፣
የንባብ ባህል ይዞታና የመጪው ክፍለ ዘመን ፈር፡፡ ደረጀ ገብሬ አርታዒ፡፡ ዐዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን
ማኅበር፣ 2001 ዓ.ም.
Onesimos Nesib.wikipedia.org
http://justus.anglican.org/resources/bio/190.html
No comments:
Post a Comment