Wednesday, January 8, 2014

ልጇን በሆዷ የቀበረችው እናት

ውብ የአማርኛ ቃል ግጥሞች ከሚነሡባቸውና ከሚያነሡዋቸው ዐበይት ጉዳዮች መካከል የረኀብንና ሞትን ያኽል ሰፊ ቦታ የሚይዝ ሌላ ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡ የዶ/ር ፈቃደ አዘዘን “ሰሚ ያጡ ድምፆች” ወይም “Unheard Voices” የተሰኘ መጽሐፍ ያነበበ ሰው የምለውን ነገር ይረዳኛል፡፡ ላለፉት ብዙ ምዕታተ ዓመት ረኃብና ሞት የታሪካችን ብቻ ሳይኾን የኪነታችን አካል እንደነበሩና ዛሬም እንዳሉ ሲታወሰኝ፣ “ኹሉን ይለውጣል” የሚባልለት ጊዜ እንዴት እኛን ሳይለውጠን (ሳንለወጥለት?) እንደቀረን እንዳስብ እገደዳለኹ፤ ልክ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ቴዎድሮስ የተሰኘው ተውኔቱ ላይ “እኮ ምንድነን?! ምንድነን?!” ብሎ እንደጠየቀው እኔም ልጠይቅ እነሣለኹ፡፡ ምን ዓይነት ከስሕተታችን የማንማር፣ ለችግር መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ ችግርን መልመድ የሚቀልለን ሰዎች ኾነን ይኾን ብዬም እጠይቃለኹ፡፡ ለማንኛውም ብዙ ሳልጨቀጭቃችኹ ዛሬ ወደማካፍላችኹ ነገር ልውሰዳችኹ፡፡ የቀነጨብኹት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “የልቅሶ ዜማ ግጥም” ብለው የዛሬ ዘጠና አራት ዓመት ገደማ ካሳተሙት መጽሐፍ ላይ ነው፡፡ እንዲኽ ይላል፡-


አንድ ዘመን ጽኑ ረኃብ ኾነና ፈረስና በቅሎ ሳይቀር እንደበሬ እየታረደ ተበላ፡፡ የንጀራስ እንኳን መብሉ ስሙ ተረስቶ ነበር ይባላል፡፡ በዚያ ዘመን አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ለርሷም የቀንድ ከብት ወይም የጋማ ከብት ወይም 1 ጥርኝ እኽል አልነበራትም ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ልጅ ብቻ ነበራት፡፡ እርሷም ሦስት ቀን ሙሉ ምናምን ሳትቀምስ አድራ በአራተኛው ቀን ካራዋን ስላ ወደ ልጅዋ ቀረበች፡፡ ልጁም የሦስት ዓመት ልጅ ነበረና ቀና ብሎ ሲያያት “ልጄ ሆይ! አኹን እኔ ብተውኽ ነገ ባንድ ስፍራ ወድቀኽ ወይም አውሬ ወይም ውሻ ሳይበላኽ አይቀርም፡፡ ነገር ግን እኔ ላንተ መቃብር ልኹን፡፡ እኔ ነገ ይኽን ጊዜ ሬሳዬን ጅብ ይቀብረዋልና፡፡” ብላ እያለቀሰች ዐርዳ በላችው፡፡

… ያች ሴት ካንዱ ወዳንዱ ስትዞር፣ ሣርም ቅጠልም እየበላች ያንን ዘመን ዘለቀችው፡፡ ዘመነ ረኃቡ ካለፈ በኋላ ነገሩ ኹሉ ትዝ አላትና እንዲኽ ብላ አለቀሰች ይባላል፡-

አላስገባም ብሎ ቢያበረኝ ወዳጄ፣
ክፉ ቀን አወጣኝ የወለድኹት ልጄ፡፡

አእምሮ እንደተነሣው ሰው መንገድ ለመንገድ እየዞረች እንዲኽ እያለች ስታለቅስ ብዙ ነጋድያን[1] አጋሰሳቸውን ጭነው ወደ መተማ ሲወርዱ አይታ “በሕያው እግዚአብሔር! አንድ ጊዜ ቁሙልኝ፡፡” አለቻቸው፡፡ በዚያም ጊዜ እንዲኽ ብላ አለቀሰች፡-

ዝባድ ለመነገድ ከመውረድ መተማ፣
ዕጣኑ[2] ይሻላል ለለት እራትማ፡፡







ምንጭ፡-
ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፡፡ የልቅሶ ዜማ ግጥም፤ ምሥጢሩ ከመጻሕፍት ጋራ የተስማማ፡፡ ዐዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያ ማተሚያ፣ 1910፡፡




[1] ነጋዴዎች
[2] ሕፃኑ

No comments:

Post a Comment