Sunday, March 30, 2014

Searching for the inclusive spirit (Reflections on the incidents of Bahirdar)

Introduction

After the death of Joseph Stalin one cadre said, "The great comrade has died but his vision lives forever!"
A passerby replied, "I wish the reverse was true."

Sunday, March 23, 2014

“ርእዮት ዓለሙ ምን ትሠራልናለች?” ("We don't need Reeyot Alemu"?)



“ኑ እንዋቀስ! ይላል ነፋሱ የአገልግሎት ዋጋቸውን በልተን በዕዳችን ያስጠየቅናቸው ግለሰቦች አሉ፡፡ ጡጫና እርግጫ የጠገቡት እነርሱ እያሉ እኛ       ግልምጫ የሚሸሽ ውርደታም ሕዝብ ኾነናል፡፡ ልጆቻችንን ሰብስበን የእነርሱን በትነናል፡፡ ቤተሰቦቻችንን ሸክፈን የእነርሱን አንከራትተናል፡፡ ቤታችንን አሙቀን የእነርሱን ጎጆ አቀዝቅዘናል፡፡” (ዓለማየኹ ገላጋይ) 


ቀኑ እሑድ ነው፡፡ በየሳምንቱ እንዲያልፉኝ የማልፈልጋቸውን ኹለት መጽሔቶች ከቢጢቆ የደምናወዜ ጭማቂ ላይ አንጀቴን አሥሬ ቦጨቅኹና ገዛኹ፡፡ በረንዳ ላይ ጥቂት ቆይቼ ወደ ቤት ገባኹና አንደኛውን መጽሔት ማገላበጥ ጀመርኹ፡፡ እበረንዳው ላይ ትቼው የገባኹት ሌላኛው መጽሔት “ስኬታማ ሴቶች” በሚል ርእስ አጅቦ የብርቱ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ፎቶግራፍ የሽፋን ገጹ ላይ ደርድሯል፤ ከሴቶቹ ውስጥም አንዷ ርእዮት ዓለሙ ነበረች፡፡ አንድ አብሬ አደጌ የኾነ የሠፈራችን ልጅ እንደ ልማዱ እቤታችን መጣ፡፡ ይኽ የዕድሜ አቻዬ ስምንተኛ ክፍልን እንኳ በቅጡ አላጠናቀቀም፡፡ ነገር ግን በልጅነታችን የክረምት ሥራ ለመሥራት ጎራ እንልባቸው ከነበሩ የመንደራችን ጫማ “ፋብሪካዎች” ጫማ መወጠር ተምሯል፡፡ አኹንም ኑሮውን በዚኹ ሥራ ይገፋል፡፡ ትምህርት እንዲቀጥል ለማድረግ እኔና ሌሎች ኹለት ሦስት ሰዎች ውትወታ ለማድረግ ሞክረን ነበር- ሰሚ ጆሮ አላገኘንም፡፡ አብሮ አደጌ በመደበኛው ትምህርት አይግፋ እንጂ ታዲያ ዘወትር ዐዲስ ነገር ለመማር ካለው ጉጉት የተነሣ ብርቱ ሬድዮ አድማጭ ነው፡፡ ከአማርኛ ውጪ የሚያውቀው ቋንቋ ስለሌለም የኢትዮጵያ ቴሌፍጀን ቋሚ ተሰላፊም ነው፡፡ 1993 ዓ.ም. ዐዲስ ዐበባ ውስጥ ተነሥቶ በነበረው ብጥብጥ እንዲኹ ከመንገድ ላይ ታፍሶ፣ በአቅራቢያችን በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ታሥሮ እንደነበር ኹላችንም እናውቃለን፡፡ ከፖሊስ ጣቢያው ጥቂት ቀናት ቆቶ ሲወጣም ፊቱና ጭንቅላቱ ቆሳስሎ እንደነበር አይተናል፡፡ ምን እንደኾነ ስንጠይቀውም “በሰባራ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ያለአንዳች ጥያቄ ደበደቡን፡፡” የሚል መልስ ነበር የሰጠን፡፡ እኛም በልጅነት ልቡና “መቼም መንግሥት ባለበት ሀገር በገዛ እጁ ራሱን እንዲኽ ሊያቆስል አይችልም” አምነነዋል፡፡

እነሆ ይኽ አብሮ አደጌ አኹን መጽሔቱን እየመለካከተ ነው፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ “ርእዮት ዓለሙ እንኳን ታሠረች! ምን ትሠራልናለች?!” ሲል ሲናገር ሰማኹት፡፡ ከእግር ጥፍሬ እስከራስ ፀጉሬ ነዘረኝ፡፡ ብልጭ አለብኝ፡፡ መጀመሪያ ጭንቅላቴ ውስጥ የመጣልኝ መልስ “አንተ ደነዝ! እንኳን ርእዮት አንተም ትሠራለኽ፡፡” የሚል ዓይነት መልስ ነበር፡፡ ወዲያው ግን “እንዴ! ያሻውን መናገር መብቱ አይደለምን?” ስል ራሴን ጠየቅኹት፡፡ “ማንም ሰው አስተያየቱን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዳለውስ አታምንምን?” ስል ጥያቄዬን ለራሴ አስከተልኹ፡፡ ወዲያውም “አምናለኹ፤ ስለዚኽም መብቱን በመጠቀሙ ልወቅሰው አይገባኝም” የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስኹ፡፡ ይኹን እንጂ ይኽ ሰው እንዴት እንዲኽ ዐይነት አመለካከት ሊያዳብር እንደቻለ ማስተንተን ጀመርኹ፡፡ 

Monday, March 10, 2014

አፄ ዮሐንስ ይዋሻሉ፡፡



በ1881 ዓ.ም. ልክ በዛሬዋ መጋቢት 1 ዕለት አፄ ዮሐንስ ራስ አርአያን፣ ንጉሥ ሚካኤልን፣ ራስ ኃይለ ማርያምን፣ ራስ አሉላን፣ ራስ መንገሻንና ራስ ሐጎስን ይዘው መተማ ላይ ከደርቡሽ ጋር ጦርነት ገጠሙ፡፡ ከጅማሮው ላይ ጦርነቱን በኃያልነት እያሸነፉ ቢቆዩም እርሳቸው ድንገት ተመትተው፣ ጦሩም ድንገት ተፍረክርኮ ሽንፈት አይቀሬ ኾነ፡፡ መጋቢት 2 ቀንም ደርቡሽም የንጉሡን ጭንቅላታቸውን ቆርጦ ወሰደ፡፡ አልቃሽም ቀጥሎ ያለውን ሙሾ ደረደረችላቸው ይባላል፡፡

አፄ ዮሐንስ ይዋሻሉ፣
“መጠጥ አልጠጣም” እያሉ፣
ሲጠጡም አይተናል በርግጥ፣
ራስ የሚያዞር መጠጥ፡፡
በጎንደር በመተኮስ፣
በደምቢያ መታረድ አዝኖ ዮሐንስ፣
ደሙን አፈሰሰ እንደ ክርስቶስ፡፡
እንዳያምረው ብሎ ድኃ ወዳጁን፣
መተማ አፈሰሰው ዮሐንስ ጠጁን፡፡
የጎንደር ሃይማኖት ቆማ ስታለቅስ፣

አንገቱን ሰጠላት ዳግማይ ዮሐንስ፡፡

(ምንጭ፡- ቦጋለ ተፈሪ በዙ፡፡ ትንቢተ ሸሕ ሑሴን ጅብሪል፡፡ ዐዲስ ዐበባ፣ እታፍዘር አታሚዎች፣ 1994)

Friday, March 7, 2014

ቤት ተከራዩ እግዜር



እግዜር፡- እንዴት ዋልሽ ልጄ? በር ላይ ያለውን “የሚከራይ ቤት አለ” የሚል ማስታወቂያ አይቼ ነው ያንኳኳኹት፡፡ ለልጄ ቤት      እየፈለግኹ ነው፡፡
እኔ፡- ቆንጆ ቆንጆ የሚከራዩ ክፍሎች አሉኝ፡፡ ዋጋቸውም በጣም ቅናሽ ነው፡፡
እግዜር፡- አይ፣ እኔ እንኳን እንደው ሙሉውን ግቢ መግዛት ነበር የምፈልገው?
እኔ፡- እምምምም… በእውነቱ መሸጥ የምፈልግ እንኳን አይመስለኝም፡፡ ማየት ከፈለግኽ ግን ግባና ክፍሎቹን ተመለካከት፡፡
እግዜር፡- እሺ፡፡
እኔ፡- አንድ ወይም ኹለት ክፍል ላከራይኽ እችላለኹ፡፡
(ቤቱን ጥቂት እየተዟዟረ ሲያይ ቆየና)
እግዜር፡- ቤቱን በጣም ወድጄዋለኹ፡፡ ኹለቱንም ክፍሎች እወስዳለኹ፡፡ ሌላ ቀን ደግሞ ጥቂት ተጨማሪ ክፍሎች ትሰጪኝ ይኾናል፡፡
እኔ፡-  ተጨማሪ ክፍሎችን ብሰጥኽ ደስ ይለኛል፡፡ ግን ደግሞ አየኽ፣ ለራሴም ትንሽ ስፍራ ያስፈልገኛል፡፡ ለዚያ ነው፡፡
እግዜር፡-  ይገባኛል፡፡ ተረድቼሻለኹ፡፡ ችግር የለም፤ መታገሥ እችላለኹ፡፡ ያን ያኽል የሚያስቸኩለኝ ነገር የለም፡፡
እኔ፡- ቆይ… አንድ ተጨማሪ ክፍል ልሰጥኽ ግን እችላለኹ፡፡ ማለቴ፣ ያው ያን ያኽል ብዙ ክፍል ስለማያስፈልገኝ… 
እግዜር፡- በጣም አመሰግናለኹ! እንደ ነገርኹሽ ቤቱን በጣም በጣም ወድጄዋለኹ፡፡ (ፊቱ ላይ የሕጻን ልጅ ፈገግታ ይጫወታል)
እኔ፡- እውነት ለመናገር፣ ቤቱን ሙሉ ብሰጥኽ ደስ ይለኛል፡፡ ግን አየኽ አንዳንድ ነገሮች ላይ እርግጠኛ አይደለኹም፡፡
እግዜር፡- ችግር የለም፡፡ አትጨነቂ፡፡ ቀስ ብለሽ ታስቢበታለሽ፡፡ እኔ ቤቱን ሙሉ ብገዛውም አንቺን ከቤትሽ አላስወጣሽም፡፡ ልጄና አንቺ ሰፋ ብላችኹ ትኖሩበታላችኹ፡፡ የአንቺ የእኔ ይኾናል፤ የእኔም የአንቺ ይኾናል፡፡ ምንም ችግር የለውም፡፡ እንዲያውም የሚገርምሽ ነገር ያኔ ቤትሽ እስከዛሬ ከነበረው ስፋት ይልቅ ይሰፋሻል፡፡
እኔ፡- እ…?! አልገባኝም፡፡
እግዜር፡- አዎን፣ አውቃለኹ፡፡ ይኽ አንቺ ራስሽ የምትደርሺበት ነገር ነው እንጂ እንዴት እንደሚኾን ላስረዳሽ የምችለው ነገር        አይደለም፡፡ የሚኾነውም ቤቱን ሙሉ በሙሉ ለእኔ ከተውሽልኝ ነው፡፡
እኔ፡- እ…እም… ማለቴ… እርግጠኛ መኾን አልቻልኹም፡፡ ትንሽ ሪስኩ በዛብኝ፡፡
እግዜር፡- ዐውቃለኹ፡፡ ይገባኛል፡፡ ግን እስኪ ሞክሪኝና እዪው፡፡ Try me.
እኔ፡- እም… እስኪ ቆይ… በደንብ ላስብበትና እነገርኻለኹ፡፡
እግዜር፡- ችግር የለም፡፡ አትጨነቂ፡፡ ዝግ ብለሽ አስቢበት፡፡ እኔም እስካኹን የሰጠሸኝን ይዤ መጠበቅ እችላለኹ፡፡ እንደነገርኹሽ ቤቱን በጣም ወድጄዋለኹ፡፡ እስካኹን በሰጠሽኝም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ 

(Source:- Peter Hannan (SJ). The Nine Faces of God)