Thursday, June 13, 2013

የቤቲ ጉዳይ፤ ሦስቱ ዐዳዲስ የኢትዮጵያ አማልክት?


ባለፈው ሰሞን ሳልከፍተው የቆየኹትን የፌስ ቡክ ገጼን ስከፍት በርከት ያሉ ጽሑፎች “ቤቲ” የምትባል ወጣት (አንዳንዶቹ ወጣትነቷንም የሚራጠሩ ነበሩ፡፡) ስለሠራችው “ጉድ” (ብትሹ በእንግሊዘኛ ብትሹ በአማርኛ አንብቡት፡፡) የሚያትቱ፣ የሚሞግቱ ነበሩ፡፡ በርከት ያሉ ሰዎችም ድንጋጤያቸውን፣ ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ “ኢትዮጲያዊነታችን በዓለም አደባባይ ተዋረደ!” ብለው ተብከንክነዋል፡፡ ቪኦኤም፣ ዶቼ ቬሌም ጉዳዩን አነሣሥተውታል፡፡ የሬድዮ መርሐ ግብሮችም አብዝተው አራግበውታል (በተለይ ታድያስ አዲስ)፡፡ ብዙዎቹ መብከንከኖች ሲጨመቁ ዛላቸው አንድ ነው- “ቤቲ ኢትዮጵያን ወክላ በኼደችበት የቴሌቪዥን ትርኢት ውስጥ እንደ ውሾችና ድመቶች የዐደባባይ ሩካቤ ፈጽማ አዋረደችን፡፡ ድሮም ስማችን አላማረም፤ አኹን ደግሞ ይባስ ብላ ኢትዮጵያ የጋለሞቶች ሀገር አሰኘችን፡፡ ኢትዮጵያዊት መምህርት ኾና እንዴት እንዲኽ ባህላችንን ታረክሳለች?!” የሚል ቁጭት፡፡ 

ቁጭታቸውን ልረዳው ብሞክርም ድንጋጤያቸውን ግን ልረዳውም፣ ልካፈለውም አልቻልኹም፡፡ እንዲያውም አደረገች የተባለውን ነገር ስሰማ ውስጤ ፈጽሞ አልደነገጠም፡፡ ያልተጠበቀ ነገርም አልኾነብኝም፡፡ ለምን?

ተወደደም ተጠላም ልጅቱ የዚኽ ማኅበረሰብ ውጤት ናት- የሥጋችን ቁራጭ፣ የአጥንታችን ፍላጭ፡፡ ማኅበረሰብ ደግሞ ከዕለተ ልደታችን ጀምሮ በእንቅስቃሴዎቻችን ኹሉ አእምሯችንን በባህሉ እየቀረፀ የምንወድደውን እንድንወድድ፣ የምንጠላውን እንድንጠላ፣ የምናከብረውን እንድናከብር፣ የምንንቀውን እንድንንቅ አድርጎ ዳግም ይወልደናል፡፡ በመኾኑም “ቤቲ ኢትዮጵያዊት ናት፡፡” ሲባል ቤቲ ኢትዮጵያውያን ስለራሳቸው ማሰብ የሚሹትን መልካም መልካሙን ብቻ ይዛ የምታውለበልብ የባንዲራ ማማ ናት ማለት ሳይኾን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ (ቢያንስ ያሳደጋት ከተሜው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ) አአምሮዋን በቀረፀበት መንገድ የምታስብ ፍጥረት ናት ማለት ነው፡፡

ጊርት ሆፍስቴድ የተባለ ሰው “ባህል የአእምሮ ሶፍትዌር ነው፡፡” ይላል፡፡ በሌላ አባባል የሰው ልጅ ሲወለድ ዐዲ ሐርድዌር ኾኖ ይወለድና ማኅበረሰቡ በአንድም በሌላም መንገድ የማኅበረሰቡ አባል የሚያደርገንን “ሶፍትዌር” ይጭንብንና በባህሉ ያጠምቀናል፡፡ ከልሙጥ ሰውነት ወደ ማኅበረሰቡ ልዩ አባልነት ዳግም ይወልደናል፡፡ ይኽን “ሶፍትዌሩንም” በየጊዜው “አፕዴት” ያደርገዋል፡፡

ብዙ ጊዜ “ባህል” ሲባል ነባርና የኾነ የጥንት ዘመን ላይ የነበሩ “ክቡራን አበው” የተፈጠረና “ሳይከለስ ሳይበረዝ” ኖሮ እኛ ዘንድ የደረሰ፣ እኛም ሳንበርዝና ሳንከልስ ወደ መጻኢው ትውልድ የምናስተላልፈው “ቅዱስ” ነገር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይኽ ግን የባህልን ምንነት ካለማወቅ የሚሰጥ የጨዋ አስተያየት ነው፡፡ ባህል ማለት የአንድ በሕይወት ያለ ማኅበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ እንጂ በሙዳይ የተቀመጠ ጨሌ ማለት አይደለም፡፡ የማኅበረሰቡ ሥርዓተ ዕሴት (value system) በተለዋወጠ ቁጥር ሲለዋወጥ የሚኖርና ሲለዋውጥ የሚያኖር እውነታ ነው፡፡ ለዚኽ ነው የቤቲ ድርጊት ያላስደነገጠኝ፡፡ በእኔ አመለካከት፣ ልጅቱ የኾንነውን እንጂ ያልኾንነውን አላሳየችንም፡፡ እዚኽ ላይ “እንዴት ብትደፍር ነው? ኢትዮጵያ የኩሩዎች፣ የደናግል (የእነ ፍቅር እስከመቃብሯ “ሰብለ ወንጌል”ና የአደፍርሷ “ጺወኔ”)፣ የሃይማኖተኞች ሀገር አይደለችምን!” ብሎ የሚቆጣ ሰው ይኖር ይኾናል፡፡

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ እንደተባለው ኩሩዎች፣ ደናግል፣ ብሉይ ከሐዲስ አስተባብረው የሚያመልኩ ሃይማኖተኞች ኖረውባት ይኾናል- ድሮ፡፡ ዛሬ ግን ኢትዮጵያ (በተለይም ደግሞ እኔ የማውቃት ከተሜዋ ኢትዮጵያ) እነርሱ እንደሚሏት አይደለችም፤ ስትኾንም ዐይቻት አላውቅም፡፡ እኔ የማውቃት ኢትዮጵያ ለሦስት አማልክት የምታጥንና የምታፈነድድ እንጂ ባለ አንድ አምላክ አይደለችም ነው፡፡ እነሆ ሦስቱን አማልክት ልጠቁማችኹ፡፡


አንደኛው አምላክ “ንዋይ” (ገንዘብ) ይባላል፡፡ በእኔ ማኅበረሰብ ውስጥ የነገሮች ትክክለኛነት የሚመዘነው ከሚያስገኙት ገቢ አኳያ ከኾነ እኮ ሰነበተ፡፡ እውነት በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ገንዘብ የማይመለክበት ቦታ የት ይኾን?! መቼም የእምነት ተቋማትን እንደማትጠቅሱልኝ ተስፋ አደርጋለኹ፡፡ አንድ ሰው የሚያደርገው ነገር ማኅበረሰቡ በይፋ አምንባቸዋለኹ ብሎ የሚደሰኩራቸውን የሥነ ምግባር ዕሴቶች እንደእምቧይ ካብ የሚንድ ቢኾን እንኳ ጓዳ ጓዳውን ሐሜት ይናፈስ እንደኾነ እንጂ ዐደባባይ ወጥቶ፣ አፍ አውጥቶ ቆሻሻን “ቆሻሻ” የሚል እምብዛም ይመስለኛል፡፡ ይኽ የአኗኗር ዘይቤያችን ከኾነ እኮ ቆየ፡፡

ጀግኖቻችን እነማን ናቸው? በኾነ አጋጣሚ ወይም ሽቀላ ከፍ ያለ ገንዘብ ያገኙ አይደሉምን? በታዋቂ ሰው (celebrity)ና በጀግና ሰው (hero) መካከል ያለውን ልዩነት ስንቱ ያስተውለው ይኾን? መቼ ነበር ያቺ “የጦብያ ቆንጆ” ተብላ የተሸለመችውና ቲቪና ሬድዮ ላይ ቀርባ “ለሌሎች ሴት ልጆች አርአያ ትኾናለች!” የተባለችው ልጅ “ምናምን-ሽን” የሚባል ኮንዶም ማስታወቂያ የሠራችውና በየፋርማሲው ላይ ያፈጠጠችብን? እኛስ ምን አልናት? ለጊዜው ያንገራገርን እንኳ ብንኖር 1000000 ብር እንደተከፈላት ወሬውን ስንሰማ (ማስረጃው ባይኖረንም) አፋችንን ለጉመን ዝም አላልንምን? እንዲያውም “ሀገረ አሜሪካን ኼዳ ሮጵላን ማብረር ተማረች፤ አይ ያለው ማማሩ!” ብለን በሬድዮን አላደናቅናትም? ደስ ይበለን! እርሷ በሮጵላኑ ሰማይ ላይ ብትሰቀልም አኹን በርከትከት ያሉ የኮንዶም አስተዋዋቂዎችን በእግሯ ተክታልናለች- ያውም እንደርሷ ቆመው ሳይኾን እየደነሱ፣ እየተወዛወዙ፣ እየተጣነዱ፡፡ ገና ደግሞ እንደአሸን ይፈላሉ፡፡ አትርሱ! እነዚኽ ኹሉ በዕድሜ የቤቲ እኩዮች ናቸው፡፡ ድኽነታችን ድኽነት ሰብእናችንን የሞራል አቋማችንን ሊነጥቀን አይገባም ነበር፡፡ ሰውነታችንን እንዲነጥቀን፣ ክብራችንን እንዲወርሰን ራሳችንን ልንሸጥንለት አይገባም ነበር፡፡ እንደ ማኅበረሰብ ቤቲን “ገንዘብ የሚያስገኝ ነገር ኹሉ ትክክል ነው!” ብለን ኖረን አሳየናት፡፡ እርሷ ደግሞ ይኽ ገንዘብ የተባለ አምላካችን ምን ዓይነት መሥዋዕት እንደሚቀበል በቴሌቪዥን አሳየችን፡፡ በቃ! አምላክን ሲያመልኩ ክብርን ጥሎ ነው!

ኹለተኛው አምላክ ደግሞ “በልጦ መገኘት/ መብለጥ” ነው፡፡ እኔ የማውቃት ኢትዮጵያ የበላይነት እንደ ውኃ የሚጠማት፣ እንደ እንጀራ የሚርባት፣ በዚኽም የተነሣ የበላይነት የምታገኝበት የመሰላትን ነገር ኹሉ ቢረባም ባይረባም ወደ ላይ አንሥታ ከማራገብ ወደ ኋላ አትልም፡፡ በኳሱም፣ በሩጫውም፣ በቴሌቪዥን ትርኢቱም፣ በዳያስጶራ ሹመቱም ከዓለም አንደኛ ከአፍሪካ ኹለተኛ እንድትኾን ትመኛለች (“ትፈልጋለች” አላልኹም)፡፡ በዚኽ የተነሣ “ውድድር” የተባለ ነገር በመጣ ቁጥር ኤፍ ኤሞቿ ውስጥ ያሉ ሰዎች ጉዳዩን ያራግባሉ፡፡ የብዙኃን ልቦችም አብረዋቸው ይርገበገባሉ፡፡ ስንቶቹ ጋዜጠኞቻችን በሬድዮ የሚያቀርቡልንን ነገር ከጥልቅ ማዳመጥ፣ ከሰፊ ንባብና ከማስተንተን (contemplation) አግኝተውት ይኾን?

እዚኽ ላይ “ምነው? ሀገራችን ከፍ ብትል ለምን ትጠላለኽ?” የሚል ጥያቄ ይነሣ ይኾናል፡፡ እኔ ሀገሪቱ ከፍ አትበል የሚል ምቀኝነትም ኾነ ጥላቻ የለኝም፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ ከፍ ያለች መኾኗን ለማረጋገጥ ውድድር ውስጥ የተባለ ነገር ውስጥ ኹሉ መግባት አለባት ብዬ አላምንም፡፡ ያሏትን ነገሮች ውበትና ጥልቀት በጭፍንና ግብታዊ “ዐርበኝነት” ሳይኾን በጥንቃቄና በእውነት በማድነቅና በመጠበቅ፣ መታረም መሻሻል የሚገባቸውንም በማሻሻል በራሷ የምትተማመንና ቀና ብላ የምትኼድ ሀገር መኾን ትችላለች፡፡ ጭፍን ዐርበኛ በመኖሩ ያይደለ በመግደሉ፣ በሀብቱ ሳይኾን በሌሎች ድኽነት፣ እርሱ ስለ በራለት ሳይኾን ሌሎች ስለጨለመባቸው ደስ ይለዋል፡፡ መኖሩን የሚያረጋግጠው በሌሎች ሞት፣ ሀብቱን የሚያረጋግጠው በሌሎች ድኽነት፣ የብርሃን ዜጋነቱ የሚሰማው ሌሎች ሲጨልምባቸው ብቻ ነው፡፡

ጭፍን የዐርበኝነት ስሜት ምን ያኽል እንደሚጫወትብን ለማሳየት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በኦሎምፒክ ሩጫ ውድድሮች ላይ የሚያሳዩት ጭንቀትና አንደኛ ካልወጡ የሚሰማቸውን መሳቀቅ መጥቀስ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በዚያን ሰሞን ስዕለት ተሳዪው የሚበዛ ይመስለኛል- እግዜር ሌሎቹን ጥሎ ኢትዮጵያውያኑን “አንደኛ” እንዲያደርጋቸው፡፡ ይኽ መቼም እግዚአብሔርን ካለመረዳት የሚመነጭም ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ የብዙዎች እግዜር ኮ እዚያ የአላዲን ተረት ውስጥ ከምናገኘውና አላዲን የሚባለው ወጣት በፋኖስ ውስጥ አሥሮት የሚዞረው፣ ሲፈልግ ደግሞ ፋኖሷን አሸት አሸት አድርጎ በመጥራት የሚሻውን ኹሉ በእጁ በደጁ የሚያደርግለት ከሃሌ ኵሉ (ኹሉን የሚችል) ጂኒ አይልለይም፡፡    
  
ሦስተኛው አምላክ ወሲብ ይባላል፡፡ ይኽ አምላክ ከሌሎቹ አማልክት ጋር በትብብር የሚሠራ አምላክ ሲኾን ሰዎች አንድም የበላይነት ጥማታቸውን ለጥቂት ጊዜም ቢኾን የሚቀዳጁበት (በተለይ ወንዶች)፣ ይኽን የወንዶቹን ጥማትና የበላይነት ቅዠት የተመለከቱ ገንዘብ ፈላጊዎች ደግሞ ብዙ ሳይለፉ ሳይደክሙ ከፍተኛ ገንዘብ የሚሰበስቡበት መንገድ አመቻችቶላቸዋል፡፡ 

ከልብስቤቶቻችንጀምሮ በአዲስ አበባ በየትኛውም አቅጣጫ ስንኼድ ሩካቤ የማይሰበክበት፣ የማይመለክበት አቅጣጫ ማግኘት ከባድ ይመስለኛል፡፡ መጽሐፎቹ (እነጠበሳ፣ እነየወሲብ ጥበብ፣ እነ78 የአሳሳም ጥበቦች፣ እነየቺቺንያ ሌሊቶች፣ወዘተ.) ቴሌፍጀኑ (ቴሌቪዥኑ?) ሩካቤን የሚያነግሡ ዘፈኖች(እነያቺነገር ጃሉድ፣ እነኼጄቴዲ አፍሮ፣ ጥበብ ማለት የሩካቤ ፍላጎትን መቀስቀስ የኾነባቸው መረን የለቀቁ ክሊፖች ወዘተ.) ልጃገረድ (ለወንድ ደግሞ ድንግልየሚለው ቃል መከበሪያ እንዳልነበር ዛሬ ማፈሪያ መኾኑ፣ ፍሬንች ኪስ ብሎ የሕንጻ ስም እስከ ማውጣት መደረሱ፣ በየሸጣሸጡ የምናየው የሥሪያ ንግዶችና የአልኮል መጠጦች ንግድ መጧጧፍ፣ በየቦታው ስንኼድ ዓይናችንን ማረፊያ ያሳጣው የኮንዶም ማስታወቂያ ወዘተማንሣት የምንችላቸው ነጥቦች ናቸው፡፡ ቤቲ ቴሌፍጀኑ ላይ ስለተሰቀለች እንጂ በየጓዳው፣ እንደ አሸን በፈሉት የማሳጅ ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች፣ የዕርቃን ክበቦች ኢትዮጵያ ድንግልናዋን የጣለችባቸው የርኵሰቷ መሥዋዕት ማቅረቢያ መሠዊያዎችዋ ናቸው፡፡ 


ቤቲ ለእኔመረኒቱን፣ “ሃይማኖተኛዪቱን በሞራል ዝቅጠት ቁልቁል እየተንደረደች ያለችውን ኢትዮጵያን በደንብ ታሳየኛለች፡፡ በቤቲ ባለ በለጬዋ ኢትዮጵያ፣ ባለ ሺሻዋ ኢትዮጵያ፣ ባለ ኮንዶሟ ኢትዮጵያ፣ ገንዘብ አምላኪዋ ኢትዮጵያ፣ ስግብግቧ ኢትዮጵያ፣ ለራሷ ክብር የሌላት ኢትዮጵያ ግዘፍ ነሥታ፣ ሥጋ ለብሳ ተገልጣለች፡፡ የገባው ካለ፣ ቤቲን ረስትቶ፣ ግብዝነቱን ትቶ ራሱን ይመልከት፡፡

No comments:

Post a Comment