ራሳችንን ኹሉን ማድረግ እንደሚችሉና
ሞት ፈጽሞ እንደማያውቃቸው ነገሮች ቆጥረን በምንኖርበት በዚህ ዓለም የኑሯችን ፍልስፍናው “ላብዛ! ልግዛ! ልብለጥ! ልሻል!” የሚል
የሐሰት ጌትነትና በሃይማኖተኛነታችን ውስጥ ሳይቀር በተሸሸገ ፈጣሪን መካድ ስለኾነ፣ እነሆ የፍቅር-የለሽ እንቅስቃሴዎቻችን ውጤቶች
አስከፊ መኾናቸውን ብናውቅም እንኳ “በአምልኮ-ርእስ” (ራስን በማምለክ) ተጠምደን “እኔ ብቻ!” በሚል የኑሮ ዘይቤ አእምሮ እንደሌላቸው
ሰዎች ከሐዘን ወደ ሐዘን እንጓዛለን፡፡
በባሕርዩ አምላክ የኾነውን እግዚአብሔርን
በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ኃይላችንና በፍጹም ዐሳባችን አምላክ እንዳይኾን “እምቢ!” አልን፤ በቃላችን ብንመሰክርም
በግብራችን በምንገልጠው ሐሰታችን አምላክ እንዳይኾነን ከለከልነው፤ በደጅ ቆሞ ለሚያንኳኳው ፍቅሩ የልባችንን በር ጥርቅም አድርገን
ዘጋንበት፡፡ ፍቅሩን እምቢ ባለችው በሐሰተኛና ጨካኝ ልባችን የተነሣ መዋደድን፣ መተዛዘንን ከእኛ አራቅን፡፡ ከዕርፍ ይልቅ ሰይፍ፣
ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍ፣ ከመሳሳም ይልቅ መነካከስ ቀለለን፡፡ ታክሲዎቻችን የመሰዳደቢያ መድረኮች፣ ድንበሮቻችን የመዋጊያ ዐውድማዎች፣
ኃላፊነቶቻችን የመጠላለፊያ ገመዶች፣ መገናኛ ዘዴዎቻችን የሐሰቶቻችን መስበኪያዎች ኾኑ፡፡
በየቀኑ ሐዘንን በጽዋ እየሞላን
እንጋታለን፡፡ እንባንም በስፍር እንጠጣለን፡፡ የእንባችን ምሬቱ ሲበዛብን አንዳችን የሌላችንን ደም በየጽዋችን እንቀላቅላለን- ምሬቱን
ይቀንስልን እየመሰለን፡፡ ነገር ግን ምሬቱ በዕጥፍ ይጨምራል፡፡ ኃጢኣትን በኃጢኣት ለማስተካከል እንሮጣለን፡፡ የልባችንን እውነተኛውን
ማረፊያ እግዚአብሔርን ስለተውነው ያለን ፈጽሞ አይበቃንም፡፡ በምኞት እንቃጠላለን፡፡ ምኞታችንን በማመንዘርና በመስረቅ፣ ማመንዘራችንንና
መስረቃችንን በመግደል፣ መግደላችንን በመዋሸት ለመጋረድ እንሮጣለን፡፡ ኹሉን የሚያይ እግዚአብሔር ግን ይህን ኹሉ ጠማማነታችንን
እያየ እንኳን የፍቅሩን መግቦት አያቋርጥብንም፡፡ አንድ ቀን ይመለሳል
ብላ ልጇን እንደምትጠብቅ እናት የልባችንን ደጅ ደጅ ይመለከታል፡፡ ልጁን እንደናፈቀ አባት እጆቹን ዘርግቶ ይጠብቃል፡፡ ይህች የተዘረጋች
ክንዱ ለማን ተገለጠች?
ይኸው እኛ ክርስቲያኖች እንኳ እግዚአብሔር
እንዲሁ ስለወደደን ብቻ የሰጠንን የፍቅሩን መስቀል በተመስጦ እያጣጣምን ከመጓዝ ይልቅ ለዕብሪታችን ምልክት አንዴ የየሀገሮቻችንን
ባንዲራ እየሰቀልንበት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የመወጋገዣ መሣሪያ እያደረግነው፣ በላዩ ላይ ያለውን ስለኛ የሞተልንን ኢየሱስ ክርስቶስን
በትምክሕታችን ቡትቶ ስንሸፍነው እንኖር የለ! የትኛውም አውጋዥ ግን “ውግዘት ያስተላለፍሁት ጥቅሜ ስለተነካችብኝ፣ ኩራቴ ስለ ተጨረፈችብኝ፣
ክብሬ ስለተነቀነቀችብኝ ነው፡፡” አይልም፡፡ ይልቁንም “እኔ ብቻ እውነተኛ ስለኾንሁ ነው፡፡ እነዚያ ደግሞ ውሸተኞች ስለኾኑ፣ ከቀጥተኛው
መንገድ ስላፈነገጡ ነው፡፡” ሲል የቃላት ፀጉር በመሰንጠቅ የሰዎችን ጆሮ በጩኸቱ ይሞላዋል፡፡ የተጠራለትን የበደሉትን ይቅር የማለት
ልዩ ክርስቶሳዊ ጥሪ በመግፋት የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዲሰብክበት በተሰጠው አትሮንስ የወንድሙን ኃጢኣት ይዘረዝርበታል፡፡ ሰዎች
በመኾናችን የሚፈጠሩብንን ድክመቶቻችንን በንስሐ እያቀናናን ከመጓዝ ይልቅ ስሕተትን በሌላ ስሕተት ለማስተካከል ስንጣደፍ እውነትን
ጥለናት ስለተጓዝን ሕይወት በሰቆቃና ስጋት፣ በጭቅጭቅና በንትርክ የተሞላች አሰቃቂ ኾነች፡፡
ከቤት ጀምሮ እስከ ሀገር ብሎም
ዓለም ድረስ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዎቻችን፣ ሰላምና መረጋጋትን ማግኛ ብለን ያስቀመጥናቸው አቅጣጫዎቻችን ኹሉ በእውነተኛው ማንነታችን
(የእግዚአብሔር ተወዳጅ ልጆች በመኾናችን) ላይ ስላልተመሠረቱ፣ ይልቁንም በየትም እንዴትም ብለን ግላዊ ወይም ድርጅታዊ ወይም ሀገራዊ
ወይም ወገናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ “በራስ-ተኮርነት” ስለምንሠራ (ስለምናፈርስ! ቢባል ይሻላል መሰለኝ፡፡) በኖርንባቸው ዓመታት
ኹሉ ምድር ጎምዛዛ እንባችንን በስፍር እንድትጠጣ አደረግን፡፡ ለእግዚአብሔር የፍቅር ጥሪ “እምቢ!” ብለን አማልክት ለመኾን ባለን
ቅዠት የተነሣ ተወዳጅ የእግዚአብሔር ፍጡራን (ሰዎች) ኾነን መኖር አቃተን፡፡ የጣልናት፣ የገፋናት የእግዚአብሔር ፍቅር ፈረደችብን፡፡
“ፍቅር ግፍ አለው፡፡” ይባል የለ፡፡ እነሆ! መንፈሳችንን በራስወዳድነታችን ጥፍንግ አድርገን አስረነው በፍርኃትና በሰቆቃ፣ በጠብና
በክርክር፣ በነፍስ ነጻነት ጥም እየተሰቃየን እንኖራለን (“እንሞታለን” ቢባል ሳይቀል ይቀራል! ደስታ የሌለበት ኑሮ ምን ኑሮ ነው?!)፡፡
“ለዘለዓለም እወድሃለሁ፡፡ እርስ
በርሳችሁ ተዋደዱ፡፡ የተወዳጅ ልጅነትህን እውነት ተቀበልና የፍቅሬ እውነት ነጻ ታውጣህ፡፡” አልኸኝ፡፡ “የምወድህ ስለውበትህ፣
ስለ ጉብዝናህ፣ ስለ ስኬትህ ወይም ስለ ትምህርትህ አይደለም፡፡ እኔ አንተን ከእነዚህ ኹሉ በፊት ዐውቅሃለሁ፡፡ የምወድድህ የእኔ
የእጆቼ ሥራ፣ ከፍቅሬ የተነሣ ያበጀሁህ የፍቅሬ መገለጫ ስለኾንህ ብቻ ነው፡፡” ብለህ የማንነቴ ትርጉም፣ የሕይወቴ ዋጋ አንተ ዘንድ
እንጂ እኔ ጋ እንዳልሆነ አሳየኸኝ፡፡
ኦ አባቴ ሆይ! እኔ እንኳን ራሴን
የማልወድድባቸው በርካታ ጊዜያት እያሉ አንተ ኹልጊዜ ትወድደኛለህ፡፡ ፍቅርህ ምንኛ ጥልቅ ነው! ጌታ ሆይ! አንተ በመረጥህልኝ፣
አንተ በቀደስህልኝ፣ አንተ ባሳየኸኝ የፍቅርና የትሕትና መንገድ ብቻ እንድጓዝ አድርገኝ፡፡ ካንተ ውጪ መንገድ፣ ካንተ ውጪ ወደብ፣
ካንተ ውጪ ማረፊያ ፍለጋ እንዳልኼድ ልቤን በፍቅርህ መልኅቅ አስክንልኝ፡፡
እኔን ከክፉውና ከሐሰተኛው እኔነቴ
ልታድን የመጣህ ወዳጄ፣ የነፍሴ አርነት፣ የመንፈሴ ጉልበት ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! እወድድሃለሁ፡፡ አመሠግንህማለሁ፡፡ ፍቅርህን
ጥዬ የዓለምን ቀንበር በአንገቴ ላይ ከመጫን እንድድን ዘወትር በፍቅርህ የምትቃጠል ልቡናን፣ በማስተዋልህም ብቻ የሚንቀሳቀሱ እግሮችን
ስጠኝ፡፡ እንደእናትህ እንደእመቤታችን ነፍሴ አንተን ብቻ ከፍ ከፍ ስታደርግ ትኑር፡፡ አሜን፡፡
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ
አሁንም ዘወትርም ለዘለዓለም
ምሥጋና ይኹን፡፡
አሜን፡፡[1]
[1] ይህችን መዝሙር በዝግታነና በዝምታ አስተንትኑልኝማ
ፍቅር የማውቀው ይኼ ነው፤
ራሱን አይወድም ጨዋ ነው፡፡
የሚያዝን ልቡ የሚራራ፣
ሐዘን ላጠቃው መከራ::
ፍቅርን ያወቀ እስኪ ማነው?
ራሱን ስለ ፍቅር ያኖረው?
ለሥጋው ክብር የማይኖር?
የተባረከ በእግዚአብሔር?
አቤት ስንት አለ በምድር ላይ፣
የበደል መዐት ገንኖ የሚታይ፡፡
ሰው በሰው እየጨከነ፣
በችግር ስቃይ እየኰነነ፣
እግዚአብሔር ይኼን ይመለከታል፣
በፈጠረው ሰው እጅጉን ያዝናል፡፡
በረኀብ ችግር ወገን ሲጎዳ፣
ማነው የሚያዝን ማነው የሚረዳ?
ጩኸቱን ሰምቶ የሚደርስለት፣
ለዚህ የበቃ ጸጋው በዝቶለት፣
እሱ ነው ጻድቅ የተባረከ፣
ልቡ የተነካ ጌታ የረዳው፡፡
ባለው ዕውቀት ላይ ዕውቀት ቢጨምር፣
ሀብቱ ቢበዛ ቢሠራ ክምር፣
ፍቅር ከሌለው ባያይ ወንድሙን፣
ታዲያ ምንድነው የቱ ነው ጥቅሙ?
እግዚአብሔር ይኼን ይመለከታል፤
የሰውን ክፋት በርግጥ ይጠላል፡፡
No comments:
Post a Comment