Saturday, January 26, 2013

ምናባዊ ጥያቄና መልስ ከቅዱሳን ጋር


በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ በተቀምጫለኹ፡፡ በግቢው አፀድ ውስጥ ኑሯቸውን ከመሠረቱት አዕዋፍና የመቁጠሪያ ጸሎት ከሚያደርሱ አንዲት እናት ዝግተኛ የመቁጠሪያ ድምፅ በስተቀር ፀጥታ ነግሦዋል፡፡ ነፍሴ በፀጥታው ውስጥ ሟሟች፡፡


የአሲዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ፣ የሳሉ ቅዱስ ፍራንቸስኮስና የሎዮላው ቅዱስ አግናጥዮስን አየኹዋቸው፡፡ ከአሲዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ አጠገብ በደስታ የሚዘልሉ በርካታ እንስሳት ይታዩኛል፡፡ የሎዮላው ቅዱስ አግናጥዮስ ደግሞ ዓይኖቹ በተመስጦ ውቅያኖስ ላይ በርጋታ ይቀዝፋሉ፡፡ የሳሉ ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ደግሞ በእጁ መጽሐፍ ይዟል፡፡ 














ያው እንደምታውቁት የመጽሐፍ ነገር አይኾንልኝምና “አባቴ፣ የያዝከውን መጽሐፍ ልየው?” ስል ጠየቅኹት፡፡ “ለአንዲት መንፈሳዊት ልጄ የጻፍኹት ነው፡፡” አለና ሰጠኝ፡፡ ርእሱ “Introduction to the Devout Life” ይላል፡፡ ውስጡን ገለጥ አድርጌ ሳይ የሚከተለውን አገኘኹ፡-


የተወደድሽ የእግዚአብሔር ወዳጅ ሆይ! 

በአንድ ሥራ መጀመሪያ ላይ የሚፈጠሩ ጥቃቅን ስሕተቶች ሥራው ወደፊት በተራመደ ቁጥር እያደጉ ይሄዳሉ፤ በስተመጨረሻም ፈጽሞ ሊታረሙ የማይችሉበት ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ ስለዚህም ከሁሉ ነገር አስቀድመሽ እውነተኛ መንፈሳዊነት ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ ይኖርብሻል፡፡

እውነተኛ መንፈሳዊነት አንድ ነው፤ የውሸትና ትርጉም የለሽ መንፈሳዊነቶች ግን ሞልተዋል፡፡ ስለኾነም እውነተኛ መንፈሳዊነት ምን ማለት እንደሆነ ለይተሽ ካላወቅሽ መንፈሳዊነት በሚመስሉ ነገር ግን የማይጠቅሙና ትርጉም የለሽ በኾኑ "ተጋድሎዎች" ተታልለሽ ጊዜሽን ልታባክኚ ትችያለሽ፡፡

ለምሳሌ፣ የመጾም ልምድን ያዳበረ ሰው  ምንም እንኳ ልቡ በጥላቻ የተመላ ቢሆንም ጾምን ስለሚያዘወትር ብቻ ራሱን እጅግ ለእግዚአብሔር የሰጠ መንፈሳዊ ሰው አድርጎ ያስብ ይኾናል፡፡ ጾሙን ላለመግደፍ እጅግ ስለሚጠነቀቅም አንዲት ጠብታ ወይንም ትኹን ውኃ አይቀምስምም ይሆናል፤ ነገር ግን በሐሜትና በሐሰት የጎረቤቱን ደም ሲጠጣ ትንሽ እንኳ ቅር አይለውም፡፡

ትዕቢትን በተመሉና እጅግ በሚያበሳጩ ንግግሮቹ በአካባቢው የተገኙትን ሰዎች ኹሉ ሰላም የሚነሣ ኾኖ ሳለ በየቀኑ ብዙ ጸሎቶችን ስለሚደግም ራሱን የእግዚአብሔር ሰው አድርጎ የሚያስብም አለ፡፡ ሌላው ደግሞ ቦርሳውን በደስታ ከፍቶ ለድኾች በደስታ ይመጸውታል፤ ለጠላቶቹ ይቅርታ ለማድረግ ግን እጅግ ከልቡ አንዳችም ቸርነት መምዘዝ አይችልም፡፡ ሌላው ደግሞ ጠላቶቹን በርግጥ ይቅር ይላል፤ ቂምም አይይዝባቸውም፤ ነገር ግን በሕግ ካልተያዘ በስተቀር የተበደረውን ፈጽሞ አይከፍልም፡፡ 

እነዚህ ኹሉ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የሰጡ መንፈሳውያን ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ እውነታው ሲታይ ግን ፈጽሞ ለእግዚአብሔር ራሳቸውን የሰጡ ሰዎች አይደሉም፡፡ መንፈሳውያን ይመስላሉ፤ መንፈሳውያን ግን አይደሉም፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈው ሳዖል ዳዊትን ሊፈልገው በመጣ ጊዜ ሜልኮል የጣዖት ምሥል አጋድማ የዳዊትን ልብስ አለበሰችውና ዳዊት አሞት እንደተኛ አሳመነቻቸው (1ኛ ሳሙ. 19፡ 11- 16)፡፡ ልክ እንደዚሁ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን በልዩ ልዩ ከመንፈሳዊነት ጋር በሚዛመዱ ውጫዊ ድርጊቶች ይሸፍናሉ፡፡ እውነታው፡ የእነርሱ ሕይወት፡ ሕይወት-አልባና የመንፈሳዊነት ቅዠት ኾኖ ሳለ ዓለም ግን ከውጪ በሚያየው የሰዎቹ ድርጊት የተነሣ ሰዎቹን መንፈሳውያን አድርጎ ያስባቸዋል፡፡


የተወደድሽ የእግዚአብሔር አፍቃሪ ሆይ! 

ሕያውና እውነተኛ መንፈሳዊነት በቅድሚያ የሚያስበው የእግዚአብሔርን ፍቅር ነው፡፡ እንዲያውም ሌላ ምንም ኹለተኛ ወይም ሦስተኛ ነገር የለውም፡፡ መንፈሳዊነት ማለት ኹልጊዜም በዙሪያችን ላለው የእግዚአብሔር ፍቅር ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ፍቅር ተራ ፍቅር አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህ መለኮታዊ ፍቅር በልባችን ውስጥ በበዛልን መጠን በእግዚአብሔር ፊት ደስ የምናሰኝ የምንሆንበት "ጸጋ" ይኾንልናል፡፡ ይህ ፍቅር በልባችን ውስጥ በሚሞላበት ጊዜ መልካም ለመሥራት ብቻ ሳይሆን መልካሙን ሥራችንን በጥንቃቄ፣ አብዝተንና ፈጥነን እንድንሠራው ያነሣሣናል፡፡ ይህ ለእግዚአብሔር ፍቅር በእያንዳንዷ የሕይወታችን ደቂቃ ደስ የሚያሰኝ ምላሽ ለመስጠት መነሣሣትም "መንፈሳዊነት" ይባላል፡፡ 


አስተውለሽ ከኾነ ሰጎኖች አይበሩም፤ ዶሮዎች አልፎ አልፎ እጅግ ዝቅ ብለው በብዙ ችግር ይበርራሉ፡፡ ንሥሮችና ርግቦች ግን ብዙ ጊዜ በቀላሉ በጣም ከፍ ብለው ይበርራሉ፡፡ ልክ እንደዚሁ ኃጢአተኞች ወደ እግዚአብሔር አይበርሩም፡፡ ይልቁንም እንቅስቃሴያቸው ኹሉ በምድር ላይ ለምድራዊ ነገሮች ብቻ ነው፡፡ መልካም የኾኑ ነገር ግን ራሳቸውን ለእግዚአብሔር በመስጠት ወደፊት ያልተጓዙ ሰዎች ደግሞ በመልካሞቹ ሥራዎቻቸው አልፎ አልፎ ወደ እግዚአብሔር ይበርራሉ፤ ይኹን እንጂ በረራቸው እጅግ ዝግተኛና አስቸጋሪ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ራሳቸውን የሰጡ መንፈሳውያን ሰዎች ግን በፍጥነትና በነጻነት በተደጋጋሚ ወደ እግዚአብሔር ይበርራሉ፡፡ 
    
እዚህ ላይ ስደርስ ልጠይቅ ወደድኹ፡፡

“አባቴ፣ ወደ እግዚአብሔር መብረር” ማለት ትርጉሙ ምንድነው?
“ወደ እግዚአብሔር መብረር ማለት…” አለና ወደ ቅዱስ አግናጥዮስ ዞሮ “ልክ እንደርሱ እግዚአብሔርን በኹሉም ነገር ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ነው፡፡”










“ከዚያስ?” የሞኝ የሚመስል ጥያቄዬን ወረወርኹ፡፡
“ከዚያማ…” አለና ወደ አሲዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ዞሮ “እንደርሱ ከሣር ቅጠሉ ጋር በእግዚአብሔር ደስ መሰኘት ይመጣል፡፡" 












"በእግዚአብሔር ደስ ስትሰኝ ደግሞ እንደርሱ ትኾናለኽ፡፡” ብሎ አንድ የሚመጣ ሰው አሳየኝ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በውብ ድምጹ እንዲህ እያለ ያንቆረቁረዋል፡-




“ሀሌ ሉያ! ለእግዚአብሔር ለዘረድአነ፤
ስብሐተ ንፌኑ ለዘፈለጠ ብርሃነ፤
አምላክነሰ አምላከ አድኅኖ፤
አአኵቶ ወእሴብሖ ወአሌዕሎ፤
እስመ ጽድቅ ቃሉ፣
እሙን ነገሩ፣
ወርቱዕ ኵሉ ፍናዊሁ፣
መንግሥቱ ዘለዓለም፡፡”[1]
ሦስቱም በምሥጋናው ተባበሩ፡፡ ድምጻቸው ምንኛ ያምራል!





[1] ለረዳን እግዚአብሔር ሃሌ ሉያ!
ብርሃንን ለይቶ ላበጀ ምሥጋናን እናደርሳለን፡፡
አምላካችን የሚያድን አምላክ ነው፡፡
ቃሉ እውነት፣
ነገሩም ታማኝ፣
መንገዱም ኹሉ ቀና ነውና
አመሰግነዋለኹ፤
ከፍ ከፍም አደርገዋለኹ፡፡
መንግሥቱም ለዘለዓለም ነው፡፡


No comments:

Post a Comment