Wednesday, December 17, 2014

አዕማደ አምባገነንነት (የአምባገነንነት ምሶሶዎች)



አምባገነንነት ምሶሶዎች አሉት፡፡ የአምባገነኖች ህልውናም በእነዚኽ ምሶሶዎች ህልውና ላይ ይመሠረታል፡፡ በዚኽ የተነሣም አምባገነኖች ሥልጣናቸውን ለማቆየት እነዚኽን ምሶሶዎች የሙጥኝ ይላሉ፡፡ ይኽ ጽሑፍም እነዚኽን ምሶሶዎች ለመተንተን ይሞክራል፡፡

1.     ድንቁርና (Ignorance)
የአምባገነኖች ዐቢይ ጠላት የሰው ልጅ የማሰብ ብቃት ነው፡፡አምባገነኖች፡ ተገዢዎቻቸውን ሲጠሯቸው አቤት፣ ሲልኳቸው ወዴት የሚሉ የአምባገነኖቹ ፈቃድ ፈጻሚ መሣሪያዎች እንዲኾኑ እንጂለምን?” እናእንዴት?” ብለው የሚጠይቁ፣ በነጻ ፈቃዳቸውና በምርጫቸው የሚንቀሳቀሱ፣ ለድርጊቶቻቸውም ሙሉ ኃላፊነት የሚወስዱ ፍጥረታት እንዲኾኑ አይሹም፡፡ አምባገነኖች በነገሡበት ዘመንና ቦታ ኹሉ በልዩ ልዩ ሥውርና ገሃድ መንገዶች የሰው ልጅ ከመሠረታዊ ፍላጎቶቹ (ምግብ፣ ዕረፍትና ርቢ) መሟላት ውጪ እንዳያስብ ይኮላሻል፡፡
አምባገነኖች ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን እጅግ የሚፈሩትም ለዚኽ ነው፡፡ ሰው ሐሳቡን በነጻነት እየገለጸ የሚወያይ ከኾነ የማሰብ ዐቅሙን ይጠቀማል፤ አማራጭ ሐሳቦችን እያቀረበ ይሟገታል፤ ይመዝናል፤ ይመርጣል፡፡ይኽ ደግሞ ተገዢዎቹን ልፍለጥኽ ሲሉት የሚጋደም፣ ልቁረጥኽ ሲሉት የሚገተር ሕይወት አልባ ግንድ ከመኾን ያወጣቸዋል፡፡ ይኼኔ አምባገነንነት ችግር ላይ ትወድቃለች፡፡ እንዲኽም ስለኾነ፣ አምባገነኖች በሚገዟት ሀገር ውስጥ የሚያስቡ ጭንቅላቶች ይቆረጣሉ፤ የሚጠይቁ አንደበቶች ይዘጋሉ፤ የሚያስተባብሩ እጆችም ይታሠራሉ፡፡ የማስተዋል መጨረሻው ስደት ወይም እሥር ወይም ሞት ይኾናል፡፡ የሰው ልጆችን በነጻነት እንዲያስቡ የሚያደርጉ ተቋማትም ኾኑ ግለሰቦች የአምባገነኖቹ በትር ያርፍባቸዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ሞጋች ምሁራን፣ ንቁ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ. እንዳያበቅል ሥርዓታዊ ማምከን (systematic sterilization) ይካኼድበታል፡፡
 
በአምባገነን ሥርዓት በተጠፈረች ሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ይኖራሉ፤ የሰውን ልጅ የሰው ልጅነቱን በምልዓት እንዲኖረው የሚያደርግ ትምህርት ግን አይኖርም፡፡ ፒኤችዲ ፋብሪካዎችየሚመረቱ በርካታምሩቃንይኖራሉ፤ ዐዋቂዎች ግን እፍኝ አይሞሉም፡፡ የብዙኃን መገናኛዎች (ሚዲያ) ይኖራሉ፤ ሥራቸው ግን የሕዝቡን ንቃተ ኅሊና እንዲጫጭ ማድረግ ይኾናል፡፡ ቴሌቪዥኖቹ ከዜና ይልቅ ዘፈንን፣ ከእውነተኛ የማኅበራዊ ጉዳዮች ትንታኔ ይልቅ የጉርምስና ድሪያዎችን፣ ወይም የብዙኃንን ቀልብ በቀላሉ የሚይዙ ስሜታዊ (sensational) ትእይንቶችን በልዩ ልዩ ቀለምና ስም ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ሬዲዮኖቹ ደግሞግባቸው ተገዢዎች ዛሬንም ኾነ ነገን በገዢዎቻቸው ዓይን ብቻ እንዲያዩ፣ በጨቋኞቻቸው ልኬት ብቻ እንዲለኩ ማድረግ ነው፡፡ በሌላ አማርኛ የአድማጮቻቸውን ጆሮ ማስባት ነው፡፡ ጆሮ ሰብቶ ምን ሊኾን?

2.ድኽነት
ኹለተኛው የአምባገነኖች መቆሚያ ምሶሶ ድኽነት ነው፡፡ ምሶሶውም ኹለት መልኮች አሉት፡፡ 

. የኑሮ ፋታ የሚሰጥ ትርፍ ሀብት
አምባገነኖች ተገዢዎቻቸው እነርሱ የማይቆጣጠሩት ትርፍ ሀብት (surplus) እንዲኖራቸው አይሹም፡፡ ምክንያቱም ትርፍ ሀብት ካለ ሰዎች የዕለት ጉሮሯቸውን ለመድፈን ከሚያደርጉት ሩጫ ፋታ ያገኛሉ፡፡ የሰው ልጅ ፋታ ሲያገኝ ደግሞ ከዕለት ጉሮሮው አለፍ አድርጎ ማሰቡ ታሪካዊ እውነት ነው፡፡ ቅድም እንዳየነው ደግሞ የአምባገነኖች ትልቁ ጠላት የሰው ልጅ የማሰብ ችሎታ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ እዚኽ ሀገር የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መሠረታዊ ፍላጎቶችን እንደምንም ብሎ ከማሟላት ሲዘልል ታይቶ ያውቃል? የመንግሥት ሠራተኞች የኾኑ ሰዎች ጡረታ ሲወጡ እንደሌላ ሀገር ጡረተኞች የማረፊያ ጊዜ አገኘኹ ብለው ደስ የማይላቸው ለምንድነው? የልጆቹን የገንዘብ ድጋፍ የማይሻ የመንግሥት ሠራተኛ የነበረ ጡረተኛ አይታችኹ ታውቃላችኹ? በሠራተኛነታቸው ጊዜ ይከፈላቸው የነበረው ገንዘብ ከእጅ ወደአፍ ብቻ ስለኾነ ለቁጠባ የሚተርፍ የላቸውም፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ለምንድነው እንዲኽ ዝቅተኛ ክፍያ እንዲያገኙ የሚደረገው? እውነት የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ሊከፍል የሚችለው ይኽን ብቻ ነው?