Tuesday, June 19, 2012

“መምሬ”[1] ኢየሱስ



ክርስቲያን ማለት “ተላውያኒሁ ለክርስቶስ” (“የክርስቶስ ተከታዮች”) ማለት እንደኾነ አበው ያስተምራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን እነዚህ ተከታዮች ከክርስቶስ ሊያገኟቸው ይፈልጓቸው ከነበሩ ነገሮች አንዱ ትምህርት ነው፡፡ በመኾኑም የክርስቶስ ተማሪዎች ነበሩ፡፡  ለዚህም ነው “ጸሎት አስተምረን፡፡” ብለው መምህራቸውን ሲጠይቁት የምናየው፡፡ ይህም እኔ “ክርስቲያን” ከኾንኹ የእነዚህ ተማሪዎች ወገን ነኝ ወደሚል ድምዳሜ ያደርሰናል፡፡ በዚህም መሠረት እርስዎ ክርስቲያን በመኾንዎ ብቻ መምህር ኢየሱስን በተመለከተ አንድ ሥልጣን ተሰጥቶዎታል ማለት ነው- ለመማር የሚፈልጉትን እንዲያስተምርዎ የመጠየቅ ሥልጣን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትም፣ ዛሬም ለዘለዓለምም የማይለወጥ ስለኾነ የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ ሳይኾን የእርስዎም መምህር ለመኾን አይደክመውም፡፡ ይልቁንም ደስ ይበልዎት! አዎን ኢየሱስ የእርስዎ መምህር ነው፡፡ ደስ ይበልዎት!

እሺ! ለአፍታ መምህር ኢየሱስ እግር ሥር ከሐዋርያቱ ጋር እንዳሉ ያስቡና ዛሬ እንዲያስተምርዎት የሚፈልጉትን ርእስ ያቅርቡለት፡፡ ዛሬ ኢየሱስ ምን እንዲያስተምርዎ ይወድዳሉ?  

ያገራችን ሰዎች ሲተርቱ “ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም፡፡” እንዲሉ እርስዎን ከመምህሩ ጋር እንዲኾኑ ካደረስኹዎት በኋላ እኔ እርሱ መማር የፈለገውን ልሰማ የ16ኛውን ክፍለ ዘመን የቤተክርስቲያን ጀግና የሎዮላው ቅዱስ አግናጥዮስን መስማት ከጅያለኹ፡፡[2] እርሱ ቀጥሎ ያለውን የትምህርት ጥያቄ አቅርቦ ነበር፤
እጅግ ተወዳጁ ጌታዬ ሆይ!
ለጋስ መኾንን አስተምረኝ፡፡
አንተን እንደሚገባህ ማገልገልን አስተምረኝ፡፡
ዋጋን ሳይቆጥሩ መስጠትን
መቁሰልን ሳይሠጉ መዋጋትን
ዕረፍትን ሳይሹ መልፋትን
ፈቃድኽን እያደረግሁ እንደኾነ ከማወቅ በስተቀር
አንዳችም ሽልማትን ሳይጠይቁ መድከምን አስተምረኝ፡፡

መምህሩም ኹሉ በእጁ ኹሉ በደጁ ነውና ይህን ተማሪውን በጥያቄው መሠረት ጥሩ አድርጎ እንዳስተማረው የሕይወት ታሪኩን የከተቡት ወዳጆቹ መስክረውልኛል፡፡



[1]መምሬ” ኢትዮጵያውያን ካህናትን ለመጥራት ከሚጠቀሙባቸው ቃላት አንዱ ነው፡፡ የቃሉ ምንጭ “መምህር” የሚለው የግእዝ ቃል ሲኾን ትርጉሙም አስተማሪ፣ የሚያስተምር ማለት ነው፡፡ “መምህርየ” ሲኾን ደግሞ የእኔ አስተማሪ የሚል ፍቺ ይይዛል፡፡ በአማርኛም “መምህሬ” ይባላል፡፡ እንግዲህ በእንግሊዘኛ contraction ብለን የምንጠራው ዓይነት የቋንቋ ኺደትን አልፎ ነው “መምሬ” ወደሚል ቃል የተለወጠው ብንል ብዙም የምንሳሳት አይመስለኝም- ቢያንስ ለዛሬ፡፡
[2] ምክንያቱም አንዳንድ ጎበዝ ተማሪዎቹ እንደነገሩኝ መምህር ኢየሱስ ጎበዝ መኾን የሚሹ ሰነፍ ተማሪዎች ከጎበዝ ተማሪዎቹ እንዲኮርጁ ይፈቅድላቸዋል፡፡ መኮረጅ የሚፈቀድባት ትምህርት ቤት እንዴት ትመቻለች ጃል!


No comments:

Post a Comment