የደቡብ አፍሪካ መንግሥት 11 የሥራ ቋንቋዎች እንዳሉት ይናገራል፡፡ ይኽ በሕግ ደረጃ
(de jury) ተቀመጠ እንጂ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እውነተኞቹ (de facto) የሥራ ቋንቋዎች እንግሊዘኛና አፍሪካንስ የተሰኘው
የደች ድቅል ቋንቋ ናቸው፡፡ ሕጉም ቋንቋዎቹ በሀገሪቱ ውስጥ ለመኖራቸው ዕውቅና ከመስጠት የዘለለ ሥራ ሲሠራ አይታይም፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች፣
በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች፣ በፓርላማ፣ በትምህርት ቤቶች ገንኖ የሚገኘው የሥራ ቋንቋ እንግሊዘኛ ነው፡፡ ሕዝቡም በዚኽ ላይ ቅሬታ ያለው
አይመስልም- ቢያንስ እኔ እንደታዘብኹት፡፡ እንዲያውም ወደ ኋላ ተመልሰን በሀገሪቱ ፀረ አፓርታይድ ትግል ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ
ስፍራ የሚሰጠውን የሶዌቶን ዐመፅ ብንመረምር የዐመፁ አንድ ዐቢይ መንሥኤ “በእንግሊዘኛ ካልተማርን” የሚለው የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን
ጥያቄ እንደነበር እንመለከታለን፡፡
ይኹን እንጂ፣ የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ለቋንቋዎቹ ግድ የለውም ማለት አይደለም፡፡ ሕዝቡ
ቋንቋዎቹ ዕውቅና እንዲነፈጉ አይፈልግም- ለአንድ ቋንቋ ዕውቅና መንፈግ ለቋንቋው ተናጋሪዎች ህልውና ዕውቅና የመንፈግ ምልክት ነውና፡፡