Wednesday, October 10, 2012

“እምቢ!”


ራሳችንን ኹሉን ማድረግ እንደሚችሉና ሞት ፈጽሞ እንደማያውቃቸው ነገሮች ቆጥረን በምንኖርበት በዚህ ዓለም የኑሯችን ፍልስፍናው “ላብዛ! ልግዛ! ልብለጥ! ልሻል!” የሚል የሐሰት ጌትነትና በሃይማኖተኛነታችን ውስጥ ሳይቀር በተሸሸገ ፈጣሪን መካድ ስለኾነ፣ እነሆ የፍቅር-የለሽ እንቅስቃሴዎቻችን ውጤቶች አስከፊ መኾናቸውን ብናውቅም እንኳ “በአምልኮ-ርእስ” (ራስን በማምለክ) ተጠምደን “እኔ ብቻ!” በሚል የኑሮ ዘይቤ አእምሮ እንደሌላቸው ሰዎች ከሐዘን ወደ ሐዘን እንጓዛለን፡፡

በባሕርዩ አምላክ የኾነውን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ኃይላችንና በፍጹም ዐሳባችን አምላክ እንዳይኾን “እምቢ!” አልን፤ በቃላችን ብንመሰክርም በግብራችን በምንገልጠው ሐሰታችን አምላክ እንዳይኾነን ከለከልነው፤ በደጅ ቆሞ ለሚያንኳኳው ፍቅሩ የልባችንን በር ጥርቅም አድርገን ዘጋንበት፡፡ ፍቅሩን እምቢ ባለችው በሐሰተኛና ጨካኝ ልባችን የተነሣ መዋደድን፣ መተዛዘንን ከእኛ አራቅን፡፡ ከዕርፍ ይልቅ ሰይፍ፣ ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍ፣ ከመሳሳም ይልቅ መነካከስ ቀለለን፡፡ ታክሲዎቻችን የመሰዳደቢያ መድረኮች፣ ድንበሮቻችን የመዋጊያ ዐውድማዎች፣ ኃላፊነቶቻችን የመጠላለፊያ ገመዶች፣ መገናኛ ዘዴዎቻችን የሐሰቶቻችን መስበኪያዎች ኾኑ፡፡

በየቀኑ ሐዘንን በጽዋ እየሞላን እንጋታለን፡፡ እንባንም በስፍር እንጠጣለን፡፡ የእንባችን ምሬቱ ሲበዛብን አንዳችን የሌላችንን ደም በየጽዋችን እንቀላቅላለን- ምሬቱን ይቀንስልን እየመሰለን፡፡ ነገር ግን ምሬቱ በዕጥፍ ይጨምራል፡፡ ኃጢኣትን በኃጢኣት ለማስተካከል እንሮጣለን፡፡ የልባችንን እውነተኛውን ማረፊያ እግዚአብሔርን ስለተውነው ያለን ፈጽሞ አይበቃንም፡፡ በምኞት እንቃጠላለን፡፡ ምኞታችንን በማመንዘርና በመስረቅ፣ ማመንዘራችንንና መስረቃችንን በመግደል፣ መግደላችንን በመዋሸት ለመጋረድ እንሮጣለን፡፡ ኹሉን የሚያይ እግዚአብሔር ግን ይህን ኹሉ ጠማማነታችንን እያየ እንኳን የፍቅሩን መግቦት አያቋርጥብንም፡፡  አንድ ቀን ይመለሳል ብላ ልጇን እንደምትጠብቅ እናት የልባችንን ደጅ ደጅ ይመለከታል፡፡ ልጁን እንደናፈቀ አባት እጆቹን ዘርግቶ ይጠብቃል፡፡ ይህች የተዘረጋች ክንዱ ለማን ተገለጠች?

Saturday, October 6, 2012

ዕረፉ፡፡ እኔም አምላክ እንደኾንሁ ዕወቁ፡፡ (መዝ. 46፡ 10)


ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጳጳስ በሚቀድሱበት ቤተክርስቲያን ውስጥ አንዲት ድብርት ፊታቸው ላይ ጎጆዋን የሠራችባቸው የሚመስሉ ክርስቲያን እናት ከፊት ለፊታቸው ተመለከቱ፡፡ በቅዳሴ ላይ እያሉ ድብርት የተከናነበውን የሴትየዋን ፊት ያስተዋሉት ጳጳስ በቅዳሴው ፍጻሜ ሴትየዋን ወደኋላ ቀረት ብለው እንዲያናግሯቸው መልእክት ላኩባቸው፡፡ ሴትየዋ እንደተባሉት ጳጳሱን ለማነጋገር ወደኋላ ቀረት አሉ፡፡ “እንደምን አሉ እናቴ? ምነው የከፋዎት ይመስላሉ፡፡” ሴትየዋ ደንገጥ ብለው “አይ እንደው ነው… እንደው ዝም ብዬ ነው፡፡ ድካሙ እርጅናው ይኾናል፡፡” ሲሉ መለሱ፡፡ ጳጳሱ ግን በዚህ መልስ አልረኩም፡፡ ይልቁንም ፊታቸው ውስጣቸውን የሚያስጨንቃቸውና የሚያበሳጫቸው ነገር እንዳለ እንደሚያሳብቅ በመጠቆም ችግሩን እንዲያካፍሏቸው አበረታቷቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ወደ ጳጳሱ ዘንድ ይቀርቡና “አባቴ፣ ጸሎት ሰለቸኝ፡፡ ታከተኝ፡፡ እንደዛሬ ሳይታክተኝ የማልደግመው የጸሎት መጽሐፍ የለም፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጀምሮ ግን የጸሎት መጽሐፌን ስከፍትና ስዘጋው ካልኾነ በስተቀር መኻል ላይ ስለምን እንደጸለይሁ እንኳ አላውቀውም፡፡ ይህም እጅግ ሲበዛ አታክቶኛል፡፡ እርግፍ አድርጌ ልተወው ነው፡፡” ሲሉ ራሳቸውን ይገልጣሉ፡፡ ጳጳሱም ሴትየዋን በጥሞና ካዳመጡ በኋላ “እናቴ፣እስኪ ጠዋት ከዕንቅልፍዎ ሲነቁ እዚያው መኝታዎ ላይ አንድ አስራ አምስት ደቂቃ ያህል ይቆዩና አካልዎን ዘና አድርገው የትንፋሽዎን ምልልስ፣ የልብዎን ምት፣ የደም ሥርዎችዎን ንዝረት፣ በዙሪያዎ ያለውን አየር በጸጥታ ያዳምጡ፡፡” የሚል መልስ ሰጧቸው፡፡ ሴትየዋ ምንም እንኳ የጳጳሱ መልስ ግራ ቢያጋባቸውም “የካህን ቃል እንዴት እምቢኝ ይባላል!” በሚል ሐሳብ ትእዛዝ እሺታቸውን ገልጸው ኼዱ፡፡