እንደኔ አስተሳሰብ "የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በደሉ፡፡" ተብሎ የተነገረንን ነገር በጥንቃቄ
መፈተሽ ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኛ ጥሩ መንገድ ሳይኾነን አይቀርም፡፡ ዘፍጥረት እንደሚተርከው አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር
ተፈጥረው መኖር ሲጀምሩ ኹሉ ነገር ሰላም ነበር፡፡ እንዲያውም እግዚአብሔር “ብዙ፤ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ የሰማይ ወፎችን፣
የባሕር ዓሦችን፣ እንዲሁም በምድር የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራን ኹሉ ግዟቸው፡፡” (ዘፍ. 1፣ 28) ብሎ ሲባርካቸው
እናያለን፡፡ "ግዟቸው፡፡" ሲል ግን በፍቅር አስተዳድሯቸው፣ በፍቅር አብራችሁ ኑሩ ማለት እንጂ እንደ ሰም
አቅልጣችሁ፣ እንደ ገል ቀጥቅጣችሁ ንገሡባቸው ማለት አልነበረም፡፡ ይልቁንም “ሰውን በአርአያችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር፡፡”
(ዘፍ. 1፣ 26) ከሚለው ዐረፍተ ነገር እንደምንረዳው ሰው የተፈጠረው እግዚአብሔር ካለመኖር ወደመኖር ላመጣቸው ፍጥረቱ ምን
ያህል እንደሚጠነቀቅ፣ ምን ያህል እንደሚያስብ ለማሳየት ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው ከተፈጠረ በኋላ ፍጥረታትን እንዲገዛ ሥልጣን
ሲሰጠው ያ ሥልጣን የእግዚአብሔር እንጂ የእርሱ አልነበረም፡፡ ቀለል ባለ አማርኛ እግዚአብሔር ፍጥረቱን እንዲያስተዳድርለት
አዳምን በእንደራሴነት (በአምባሳደርነት) ሾመው ማለት ነው፡፡ እንደራሴ ደግሞ እንደምታውቁት ሥራው የሾመውን ንጉሥ መልእክት
ማስተላለፍ ነው፡፡ የእርሱ ሥራ የንጉሡን ክብር መወከል ነው፡፡ አዳምም እንዲህ ዓይነት ሥራ ነው የተሰጠው- እግዚአብሔር
መልካም አድርጎ ለፈጠራቸው ፍጥረቱ ያለውን የመጋቢነት፣ የጠባቂነት፣ የተንከባካቢነት፣ የእናትነት ኃላፊነት በፍጥረታቱ መካከል
ማሳየት፡፡ “ወስዶ እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት በኤድን ገነት አኖረው፡፡” ይል የለምን? (ዘፍ2፡ 18)
እንደራሴ ንጉሥ አይደለም፡፡ የእንደራሴነት ምንጩ ንጉሥ ነው፡፡ ንጉሥ ከሌለ “እንደራሴ” ለሚለው ቃል ፍቺ
መስጠት አይቻልም፡፡ የእንደራሴ ኑሮ ማዕከሉ፣ መሠረቱ ንጉሡ እንደኾነ ኹሉ አዳምም በእርሱ ውስጥ እግዚአብሔር ብቻ እንዲታይ፣
በውስጡ እንደ መስታወት የእግዚአብሔርን ብርሃን እንዲያንጸባርቅ ነበር የተጠራው፡፡ እንደራሴው ከንጉሡ ውጪ ትርጉም አይኖረውም፤
ንጉሡ የህልውናው መሠረት ነው፡፡ ንጉሡ የለም ማለት እንደራሴው የለም ማለት ነው፡፡
እንደራሴነት ጥሩ ነገር ነው፤ ነገር ግን የህልውናው ዓላማም ኾነ ትርጉም ንጉሡን መወከል፣ የንጉሡ ምልክት መኾን ብቻ መኾኑ መረሳት የለበትም፡፡ ሰይጣን ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ያቀረበው ፈተና ይህን የተፈጠሩበትን ዓላማ እንዲዘነጉ ማድረግ ነበር፡፡
የሰው ልጅም በፈተናው በመሸነፍ ንጉሡን ከመወከል ይልቅ በንጉሡ ቦታ መታየትን መረጠ:: ንጉሡን ከመወከል እንደ ንጉሡ መኾንን ጎመዠ፡፡ በዚህ ንጉሡን የህልውናው ማዕከል ከማድረግ ይልቅ ራስ-በቅ (self-sufficient)ና ፍጥረት ኹሉ ሊያገለግለው የሚገባው ማዕከለ ፍጥረትነትን ጎመዠ፡፡ ይህ መጎምዠትም ፍጻሜ ሊያገኝ ይችል የነበረው የህልውናው መሠረት የነበረውን የንጉሡን ሥልጣን በመካድ ላይ ነበር፡፡ በመኾኑም መጎምዠቱን ለማርካት የንጉሡን ማዕከለ ፍጥረትነት፣ የንጉሡን እውነተኝነት ካደ፡፡ ነገር ግን ንጉሡን ሲክድ የእርሱ የእንደራሴነት ህልውናው እንደሚያከትም አልተገነዘበም፡፡ ንጉሡን ሲክድ እርሱ የማን አምባሳደር ሊባል ይችላል? በዚህም የተነሣ በዚያች በምልዐት እንዲኖር ያደረገውን የኑሮውን ማዕከላዊ ነጥብ ከኑሮው በነቀለባት ቅጽበት በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቀዳዳ ተፈጠረ፡፡ ማን ነኝ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ጠፋ፡፡ ትርጉም አልባ ሕይወት ደግሞ ከመርግ ይልቅ ትከብዳለች፡፡ ስለዚህም ይህን አስፈሪ ትርጉም አልባነት "ዛፍ ሥር" በመጠለል ሊሸፍነው ሙከራ ሲያደርግ እንመለከታለን፡፡ "ዛፍ" መጥፎ አይደለም፡፡ ይልቁንም "መልካም" ከተባሉት የእግዚአብሔር ፍጥረት መካከል አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ብቻ ትርጉም የሚኖረው ሕይወታችንን ከባዶነቱ በፈጣሪ ሳይኾን እንደኛው በኾነው በሌላ ፍጡር "በዛፍ" ልንሸፍነው ስንሞክር፣ በፍጥረቱ መልካም የነበረው ዛፍ ለእኛ የውርደት ምልክት ይኾንብናል፡፡ ዛፉ ራሱ የህልውናውን ትርጉም የሚያገኘው ህልውናውን ባስገኘለት በፈጣሪው ነውና በምንም መልኩ የሌላ ፍጥረት ህልውና ትርጉም ሊኾን አይችልም፡፡
እንግዲህ ይህ ባዶነትን በጸጋው ብርሃን ሕይወታችንን ምሉዕ በሚያደርጋት በፈጣሪያችን ሳይኾን በሌሎች
መልካም መስለው በሚታዩን ፍጡራን ነገሮች (ከመጠን በላይ ሀብት በማካበት፣ በምቾት፣ በምግብ፣ በወሲብ፣ በጫት፣ በትንባሆ፣
በመጠጥ ወዘተ.) ለመሙላት የሚደረግ ጥረት የተጀመረው ያኔ ነው፡፡ የፈጣሪ ቦታ ግን በየትኛውም ፍጡር ሊሸፈን አይችልምና እርሱ
እስኪይዘው ድረስ በማንም ሊያዝ አይችልም፤ ክፍት ኾኖ ይኖራል እንጂ፡፡
አዳምና ሔዋን የተሰጣቸው አልበቃቸው ብሎ ሰጪውን ራሱን እነርሱ ሊገዙት ፈለጉ (ደግነቱ እርሱም ይህንን ዐውቆ የእነርሱን ሥጋ ለብሶ መጣላቸውና ልጃቸው ይሁዳ በሠላሣ ብር ሸጠላቸው)፡፡ ማዕከለ ዓለም (the center of the whole universe) እግዚአብሔር መኾኑ ቀርቶ እነርሱ እንዲኾኑ ተመኙ፡፡ ካስተዋልነው ኦሪት ዘፍጥረት ይህንን የዓለም በሽታ በግልጥ ይጠቁመናል፡፡ እባብ ፍሬውን ለሔዋን ሲያሳያት “ሴቲቱም ፍሬው ለዓይን የሚያምር፣ ለመብላትም የሚያስጎመዥ እንደኾነ ዐየች፡፡” ይላል፡፡
በቃ! መጎምዠት በሚለው ቃል ውስጥ የምጣኔ ሀብት (አንዳንዶች "ሥነ ስስት" ብለው
ይጠሩታል/ ኢኮኖሚክስ) መምህሮቻችን “human wants are unlimited.” ብለው ያስተማሩን ነገር በጥንታውያን አበው
ብርዕ ዘፍጥረት ውስጥ ቁልጭ ብሎ ተጽፎልናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገራቸው ዐበይት እውነቶች አንዱ (በእኔ እምነት ዋናው
ሰብአዊ ጉዳይ) ይህ የሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ የተጠመደበት “የላብዛ ልግዛ” የኑሮ ፍልስፍና እንዴት
ከቀውስ ወደ ቀውስ እንደሚመራ ማሳየት ይመስለኛል፡፡
ኢትዮጵያውያን አበውና እማት “ዓለም ዘጠኝ ናት! ጎዶሎ! ሞልታ የማታውቅ!” ሲሉም በዘጠኙ ቀዳዳዎቹ
ሲያስገባ ሲያስወጣ የሚኖረውን ቀዳዳውን በርሜል የሰው ልጅን ማለቂያ አልባ ፍላጎት ሲያመለክቱ እንደኾነ አምናለሁ፡፡ ፍላጎትህን
ለማሟላት ትሮጣለህ፤ እስክትይዘው የሚያረካ ይመስልሃል ስትይዘው ግን ውኃ የማይቋጥር ኾኖ ታየዋለህ፡፡ ሌላ ውኃ የሚቋጥርልህ
የመሰለህን ደግሞ ታባርራለህ እዚያም ስትደርስ እንዲሁ እርካታ የለም፡፡ እድሜህን እንዲሁ ስትሮጥ ትፈጽመውና በሕይወትህ ምዕራፍ
መዝጊያ ላይ ስትደርስ እንደ ሾፐንአወር የሚከተለው ምሬት ብቻ ይተርፍሃል፡፡
In early youth, as we
contemplate our coming life, we are like children in a theatre before the
curtain is raised, sitting there in high spirits and eagerly waiting for the
play to begin. It is a blessing that we do not know what is really going to
happen. Could we foresee it, there are times when children might seem like
innocent prisoners, condemned, not to death, but to life, and as yet all
unconscious of what their sentence means.
…If two men- who were
friends in their youth- meet again when they are old, after being separated for
a life-time, the chief feeling they will have at the sight of each other will
be one of complete disappointment at life as a whole; (Schopenhauer:
Studies on Pessimism)
ወንጌል “እውነት ነጻ ታወጣችኋለች፡፡” (ዮሐ. 8፣ 32) ስትል ስሰማት “ኢየሱስ ጌታ እንደኾነ በልብህ
ብታምን በአፍህ ብትመሰክር” (ሮሜ 10፣ 9) ብላ ስታስተምር ሳደምጣትም የምትነገረኝ እውነት ይህንኑ ነው፡፡ “ጌታ” የሚለው
ቃል በወንጌል ውስጥ ስናየው እንደው የሩቅ ጌትነት ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም በአንድ ቤት ውስጥ የቤቱ ጌታ የቤቱ
ማዕከል እንደኾነና በቤቱ ውስጥ ያለው ኹሉ ከልሒቅ እስከ ደቂቅ እንደሚታዘዙለት ኹሉ ኢየሱስ ጌታህ ከኾነ መጀመሪያ የምትማረው
እውነት አንተ የራስህ ወይም የሌሎች ጌታ አለመኾንህን ይኾናል፡፡ ይልቁንም አንተም ኾንህ ሌሎቹ የዓለሙ ነዋሪዎች የህልውናችሁ
መሠረት ወደኾነው ወደ ቤቱ ማዕከል የምታመለክቱ ቅስቶች ትኾናላችሁ፡፡ ስለዚህም አንተ ወይም ሌሎች ልታሟሉት የሚገባችሁ ፈቃድ
የአንተን ወይም የእነርሱን ሳይኾን የቤቱን ራስና ኹሉ አንድ የሚኾበትን መጋጠሚያ የኢየሱስን ነው፡፡ የእርሱ ፈቃድ ደግሞ እርሱን
እንድንወድደውና ፍጥረትን ኹሉ ደግሞ በእርሱ የፍቅር ዓይን እንድንመለከትለት ነው፡፡
በሰማያት የኾነው የሰማዩ አባታችን ፈቃድ በሰማይ እንደኾነ እንዲሁም ደግሞ በምድር የሚኾነው ይህን ጊዜ
ብቻ ነው፤ ማለትም እኛ ምንም እንደኾንንና እርሱ እግዚአብሔር ግን “የምንኖርበት፣ የምንንቀሳቀስበትና ያለንበት” (ሐዋ.
17፡28) የህልውናችን መሠረት፣ የመገኘታችን ምክንያትና የሕይወታችን ፍጻሜ እንደኾነ መቀበልና መኖር ስንጀምር፡፡ “የአባቴን
ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ አቤቱ አቤቱ የሚለኝ ኹሉ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፡፡” ብሎ ጌታ ኢየሱስ ያስተማረን የአባቱን ፈቃድ
ይኸውም አምላክነቱን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ኃይላችን እንድንቀበልና (አዳም “አልቀበልም!” ያለው እርሱን
ነበራ!) የእርሱ እንደራሴዎች ኾነን፣ የእርሱን ብርሃን በሰው ኹሉ ፊት አንጸባርቀን ለመኖር እንድንችል ነው፡፡ “የምንኖረውና
የምንንቀሳቀሰው፣ ያለነውም በእርሱ” (ሐዋ. 17፡ 28) መኾኑን አምነን እርሱን የህላዌያችን መሠረትና ማዕከል፣ መነሻና
መድረሻ፣ አልፋና ዖሜጋ አድርገን መኖር ስንጀምር ብቻ ከተጠመድንበት “እኔ” የሚባል መሥዋዕት የማይጠግብ ጣዖትና እርሱ
ከሚጭንብን ዐለምን ኹሉ ለፍላጎታችን ማርኪያ እንደተፈጠረ የመቁጠርና ኹሉን በቁጥጥራችን ሥር ለማዋል የመፈለግ የእርካታ ማጣት
ቀንበር ነጻ እንወጣለን፡፡ ኹሉን ለእግዚአብሔር ብቻ እናደርጋለን፤ ኹሉን በእግዚአብሔር በኩል እናያለን፡፡
ጌታ ኢየሱስ “ስለእኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ኹሉ ግን ያድናታል፡፡” (ሉቃ. 9፣ 24) ያለን “እኔ”
የምትባለውን ብዙዎቻችን በማወቅም ባለማወቅም የምናመልካትንና ለምቾቷ የምንደክምላት፣ ለፍላጎቷ የምንገብርላት፣ ለግዛቷ
የምንዋጋላትን ጣዖት እንድተዋት ነው፡፡ “እኔ”ን ስተዋትና ራሴን ጨምሮ ፍጥረትን ኹሉ በእግዚአብሔር በኩል መመልከት
ስጀምር ሌሎችን “መግዛት”፣ “መንዳት”፣ “በቁጥጥር ሥር ማዋል”፣ “የግል ንብረት ማድረግ” ከሚባለው ፍጻሜ አልባ
አድካሚ የቁልቁለት ሩጫ እገላገላለሁ፡፡ እፎይ! እላለሁ፡፡ ፍጥረትን ኹሉ ለፍላጎቴ መፈጸሚያ፣ “ለክብሬ” እንዲንበረከኩ ሳይኾን
ልክ እንደኔው በመኖራቸው የእግዚአብሔር ክብር እንዲገለጥባቸው፣ ብርሃኑ እንዲታይባቸው የተፈጠሩ መቅረዞች መኾናቸውን
አስተውላለሁ፡፡[i]
በፍጡርነቴ ያለብኝ ኃላፊነትም ከእነዚህ ፍጡራን ዘመዶቼ ጋር በፍቅርና በደስታ፣ ከአንዱ ምንጭ ከእግዚአብሔር አብ የሚፈልቀውን
የመንፈስ ቅዱስ የሕይወት ዘይት ይዞ የኢየሱስን ብርሃን እያበሩ መኖር ብቻ ይኾናል፡፡
እንዲህ መኖር ስትጀምር ረዥምና አጭር እድሜ፣ ሕመምና ጤንነት፣ ሀብትና ድኽነት፣ የዐለም ክብርና ውርደት ለአንተ
ልዩነት አይኖራቸውም፤ በኹሉም ውስጥ እግዚአብሔርን ታየዋለህና፡፡ ሰው ክርስቲያን ሲኾን በኑሮው እንዲያሳየው የሚፈለገው ሕይወት
እንዲህ ያለው እግዚአብሔርን ማዕከል አድርጎ የመኖር የአኗኗር ዘይቤ ነው፡፡ ክርስቶስን መስሎ መኖር ማለትም ይኸው ነው-
ኢየሱስ ለአብ ፈቃድ ብቻ እንደኖረ አንተም ለአብ ፈቃድ ብቻ እንድትኖር፡፡
የሰው ልጆች በዚህ ክርስቶሳዊ የአኗኗር ዘይቤ ቢመሩ እንኳን በክርስቲያኖች መካከል ያሉ ትዕቢትና
አለመናበብ የፈጠሯቸው ልዩነቶች ይቅሩና ሕዝብና አሕዛብ፣ ተገዳይና ገዳይ፣ አባራሪና ተባራሪ፣ ባርያና ጌታ፣ አይሁዳዊና
ግሪካዊ፣ ወንድና ሴት የሚባሉ ማለቂያ አልባ የዓለም ክፍፍሎች ይጠፋሉ፡፡ ለጥቂቶች የማይጠቅም የወርቅ ሐብል ለመሥራት ለኹሉ
የሚኾነውን የውኃ ምንጭ መመረዝ ያበቃል፡፡ ፍሬውን ለመብላት ሲሉ የማፍሪያ ጊዜውን በትዕግስት መጠበቅ ሳይኾን ዛፉን መቁረጥ
ከሰው ልጅ ዘንድ ይወገዳል፡፡ ሰይፉን ቀጥቅጦ ማረሻ ያደርገዋል እንጂ ትራክተሩን መድፍ አይጭነውም፡፡ ስግብግብነት ይሞታል፡፡
ጨካኝነት በደግነት ይገደላል፡፡ ኩራት በትሕትና ይሻራል፡፡ ኹላችን የክርስቶስ ልብ ይኖረናል (1ኛ ቆሮ. 2፡ 16)፡፡ ኦ!
ይህ ልብ ምንኛ ሰላማዊ ነው!
በቃ! የሰው ልጅ ልቡ ያርፋል፡፡ የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ አውጉስጢኖስ “ጌታ ሆይ! አንተ ላንተነትህ
ፈጥረኸናልና ባንተ እስኪያርፍ ድረስ ልባችን ዕረፍት አልባ ኾኖ ይኖራል፡፡” እንዳለው በእርሱ በፈጣሪያችን እናርፋለን፡፡
ይህ መንገድ ግን የእግዚአብሔር እንጂ የዐለም መንገድ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ዐለም የምትቃወመው
ምክንያቱም ስሕተቷን ያጋልጥባታልና፤ ዋሾነቷን ይመሰክርባታልና፡፡ ይህንን መንገድ ለሚመርጥ ሰው ዐለም የምታቀርብለት ዙፋን
መስቀል ይባላል፡፡ ይህን መስቀልም በብዙ መንገድ በየሰዉ ልክ እንደምታበጀው ይነገርላታል፡፡[ii] ስለዚህም
ነው እንደ ሔኖክ አካኼዱን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ ብቻ የሚፈልግን ሰው በእያንዳንዷ የሕይወቱ ሰከንድ እግዚአብሔርን ትቶ
“እኔን” ማዕከል ያደረገ ሕይወት እንዲመራና “እንደእግዚአብሔር እንዲኾን” ለሔዋን የቀረበው የኃጢኣት ግብዣ ሲቀርብለት
የሚታየው፡፡
ለዚህ ነው እግዚአብሔርን የሕይወትህ ማዕከል አድርገህ ለመኖር ስትሞክር ሲያይህ “ከእግዚአብሔር እስር ነጻ
መውጣት” ያሉትን “ጠቀሜታዎች” በሚዘረዝሩ ወይም እግዚአብሔር እንዴት አንተን አምላክ እንዳትኾን፣ እርካታ እንዳታገኝ፣ በደስታ
እንዳትፈነጭ እንደከለከለህ በሚሰብኩ ማስታወቂያዎች ሊያባብልህ ሲሞክር የምትመለከተው፡፡ እግዚአብሔር የሌለበትና አንተ “የነገሥህበት”
ሕይወት የሚያስገኙልህን ክብርና ምቾት እያሳየ “ለእኔ ብትሰግድልኝ ይህን ኹሉ እሰጥሃለሁ፡፡”
ይልሃል፡፡ ይህንን ፈተና ስታመልጥ ደግሞ አንተ ብቻ “በኋላቀርነት” መንገድ ላይ ተጣብቀህ እንደቀረህ ይነግርሃል፡፡ “ሰው ኹሉ
የሚያደርገውን ነገር አንተስ አንዴ እንኳን ብትሞክረው ምናለበት?” እያለ ዐይንህን ከእግዚአብሔር ላይ ነቅለህ አንተን “አምላክ
(ደስተኛ፣ ስኬታማ፣ የተፈራህ፣ የተከበርህ፣ የተወደድሽ፣ የተዋብሽ ወዘተ.) ታደርግሃለች!” በሚልህ “ፍሬ” ላይ
እንድታተኩር ይጎተጉትሃል፡፡
ይህን ጊዜ አደራህን ተጠንቀቅ! ፍሬዋ “መጎምዠት” የሚባል ታላቅ ቀዳዳ በሕይወትህ በመክፈት ከእግዚአብሔር
ጋር ኾነህ የምታገኘውን ሰላም፣ መረጋጋት፣ ፀጥታ፣ ፍቅር ከሕይወትህ እንዲጠፉ ታደርጋለችና፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለዚህ ነው “እንደ
እባብ ብልኅ እንደርግብ የዋኅ” እንድንኾን የነገረን፡፡ ማባበሉንም ማታለሉንም ስትነቃበት ደግሞ ማስገደድና ማስፈራራት ሌላው
አማራጭ ኾኖ ይመጣል፡፡ ከሽሙጥ እስከ ሽጉጥ ይመዘዛሉ፡፡ ከስድብ እስከ ድብድብ፣ ከመወገዝ እስከ መገዝገዝ የሚደርሱ ጎዳናዎች
ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ እንደጥላ በኼድክበት ይከተሉሃል፡፡ “ላብዛ- ልግዛ፤ ልመለክ-ልከበር” ከሚለው ከአንተነትህ ጀምሮ በ“ላብዛ
ልግዛ” ፍልስፍና እስከተመሠረተውና በዚሁም ፍልስፍና እስከሚኖረው ሥርዓተ ዐለም ድረስ በጠላትነት ይቆሙብሃል፡፡ ያሳቅሉሃል፤
ይሰቅሉሃል፤ ይገድሉሃል፡፡ ለዚህም ነው ጌታ ኢየሱስ ዕለት ዕለት ኹላችንም የየራሳችንን መስቀል ተሸክመን ለመጓዝ ዝግጁዎች
እንድንኾን የነገረን፡፡ ደግሞም “በዐለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፡፡” ብሎናል፡፡ ይኹን እንጂ፣ መከራ አለባችሁ ብሎ ብቻ
አላቆመም፡፡ “ግን አይዟችሁ እኔ ዐለምን አሸንፌዋለሁ፡፡” (ዮሐ. 16፣ 33) ሲል ብሥራት አሰምቶናል፡፡ ስለኾነም ዐለም
ቢሰቅልህም፣ ቢገድልህም ሞተህ አትቀርም፡፡ ደስ ይበልህ! እንደወደድከው፣ እንደተከተልከው ጌታህ ኢየሱስ ክርስቶስ
ትነሣለህ፡፡ ዳግመኛም አትሞትም፡፡ ይልቁንም እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፍጹም ነፍስህ “ነፍሴ” (“እኔን”
ሳይኾን) “እግዚአብሔርን ታላቅ ታደርገዋለች፡፡” ለማለት ትበቃለህ፡፡[iii]
የእመቤታችን በረከቷ ይደርብን፡፡ ረድኤቷ፣ ጸሎቷ፣ አማላጅነቷ ይደግፈን፡፡
[i] የአሲዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ
ማኅሌተ ፍጥረትን የደረሰው እግዚአብሔርን የማፍቀር ፀሐይ በሕይወቱ ስለወጣችለት ነበር፡፡ እርሱ በዚያ ማኅሌቱ ውስጥ የሚያሳየን
ዐይነት እይታ ሊኖረን የሚችለውም ዐይኖቻችን ፍጥረትን ከሀብት ወይም ከጥቅም አኳያ ሲያጨነቁሩ ሳይኾን በእግዚአብሔር በኩል መመልከት
ሲችሉ ብቻ ነው፡፡
[ii] እዚህ ቦታ ላይ በዚህ በጾመ ፍልሰታ የተለዩን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ለሚመረቁ ደቀ መዛሙርት ይሰጡ ከነበረው ውብ ምክር ጥቂት ቀንጭበን እንስማ፡-
የተወደዳችሁ ልጆቼ!
… ዓለም አበባ ይዛእንደማትቀበላችሁ ዕወቁ፡፡ ይህ በእናንተ የተጀመረ ሳይሆን የዓለም መገለጫዋ መሆኑን አትዘንጉ፡፡ልዩ ልዩ ነቀፋና ስደት ሲመጣባችሁ ከዓለም እንደ ተጣላችሁ አትቍጠሩት፡፡ እንዲያውም ከዓለምጋር እንደተዋወቃችሁ ቍጠሩት፡፡ ዓለም እንደዚህ ናትና፡፡ ጎበዝ የሚባለው ሳይቀር በመገፋት ውስጥበኀዘን ይጎዳል፡፡ የሚታይ ተስፋም እያጣ በብቸኛነት ይንገላታል፡፡ ይሁንና ሰው መተማመኛየማይሆን የሸምበቆ ምርኵዝ መሆኑን ቃሉ ይነግረናል /ኢሳ.36፤6/፡፡ ስለዚህ በሁሉም ነገር ውስጥየጠራችሁን ጌታ ክርስቶስን ተመልከቱ /ዕብ.3፤1/፡፡ የተቀበላችሁትን ለመስጠት ብቻ ሳይሆንያልተቀበላችሁትንም ለመስጠት ፈቃደኞች ሁኑ፡፡ ፍቅርን አላያችሁ ከሆነ ከእናንተ ይልቅ የፍቅርንረሀብ የሚያውቅ የለምና ፍቅርን ስጡ፡፡ የሚያዝንላችሁ አባት አላገኛችሁ እንደሆነ ለሚጠጓችሁእናንተ ደግሞ አዛኝ አባቶች ሁኑ፡፡ ተራራውን ስትጨርሱ መስክ እንደሚያጋጥማችሁ እያሰባችሁበተራራው አትዘኑ፡፡ እናንተ ዱር መንጣሪዎች ናችሁና የተመቸ ቦታን ፍጠሩ እንጂ ምቹ ቦታንአትጠብቁ፡፡ የደረሰባችሁ ችግርም እስከ ዕድሜአችሁ ፍጻሜ የምትናገሩትን ትምህርት ይሰጣችኋልናአትበሳጩ፡፡ ከምትፈልጉት ነገር ይልቅ ያገኛችሁት ይበልጣል፤ እርሱም የሰማይ ዜጎች መሆናችሁነውና ደስ ይበላችሁ! (ምንጭ፡-
www.betepawlos.com)
[iii] መነሻ መጻሕፍት፡-
ሦስቱ መጻሕፍተ መነኮሳት፡፡ ማር ይስሐቅ፡፡
አባ ወልደ ጊዮርጊስ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፡፡
St. Augustine of Hippo. Confessions.
St. Ignatius of Loyola. Spiritual Exercises.
Gerard Hughes (SJ). God of Surprises.
Peter Hannan (SJ). Nine Faces of God.
H. Staffner. What Does it Mean to Be Christian?
Arthur Schopenhauer. Studies on Pessimism.
Dear Mehari,
ReplyDeleteEgziabhier bemneth Yaxnah.
Amen.
DeleteDear Mehari,
ReplyDeleteI have found this article very interesting and clearly explained. If it is your good brotherly will I want to translate it to ( French, Dutch, and Tigriga) and share it with others.
I can send you the draft before using it in any way.
Expecting your good will
Daniel ( Amsterdam)
Dear Daniel,
DeleteIt is a great pleasure to have you reading the article. I didn't think it would be that much interesting to others. I was just sharing what I learnt from my recent readings. May the Lord be with you in your translation works. You can translate, share (both in print and online), rewrite or edit or paraphrase. Indeed it is a great honor to me to serve as a vessel and to have a helper like you for what I learnt from the servants of the Lord.
Dear Mehari (old friend), this article is a wonderful masterpiece. Keep writing dear.
ReplyDeleteHiruy