ቀጥሎ የቀረበላችሁ ጨዋታ ከባለ ቅኔው መንግሥቱ ለማ አባት ከአለቃ ለማ ኃይሉ የተገኘ ነው፡፡ ሙሉ ጨዋታቸውን “ትዝታ ዘአለቃ ለማ” ከተሰኘው መጽሐፍ ታገኙታላችሁ፡፡ የዚህ ጡመራ መታሰቢያነቱ እነርሱ ከሚያውቁት ውጪ ሌላ ዕውቀት ያለ ለማይመስላቸው፣ “መመራመር ብርቁ” ለሆኑ የዐውደ ምሕረትም ሆነ የዐውደ ዕውቀት “አስተማሪዎች” ይሁንልኝ፡፡
ደጃች ኃይሉ የሸደሆ ገዥ፣ ደጃች ወንዴ ደግሞ የመቄት ገዥ ነበሩ፡፡ ደጃች ኃይሉ የተማሩ ሲሆኑ፣ ደጃች ወንዴ ግን አልተማሩም ነበር፡፡ ደጃች ከጣቢሽ የተባሉት ደግሞ ሁለቱንም ግዛቶች በአንድነት ይገዙ ስለነበር የሁለቱም ደጃቾች የበላይ ነበሩ፡፡
ሁለቱ ደጃቾች ወደ ደጃች ከጣቢሽ ይሄዳሉ፡፡ ቤተክርስቲያኑ ጊዮርጊስ ነው፡፡ ሁለቱም በቤተክርስቲያን ተገኝተው ይጸልያሉ፡፡ ደጃች ኃይሉ ዳዊት አውጥተው ዳዊታቸውን ይደግማሉ፡፡ መልኩንና ይህን የመሰለውን ሁሉ በመጽሐፍ ይደግማሉ፡፡ ደጃች ወንዴ ደግሞ ትምህርት የሌላቸው ናቸውና “ቅዱስ ጊዮርጊስ የአባቴ አምላክ! ፈጥረህ የት ትጥለኛለህ?” እያሉ ያለ መጽሐፍ በቃል ይጸልያሉ፡፡ በኋላ ሁለቱም ተያይዘው ደጃች ከጣቢሽ ወዳሉበት ይወጣሉ፡፡ ከዚያ ደጃች ወንዴ “ደጃች ኃይሉ፣ መማር ለምን ይበጃል?” አሉ፡፡ ተንኮለኛ ነህ ለማለት ነው፡፡